ቀጥታ፡

ጠንካራና ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ለመስጠት ከአጋር አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 25/2017(ኢዜአ)፦ጠንካራ እና ጥራቱን የጠበቀ የጤና አገልግሎት ለመስጠት ከአጋር አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ፥ አንድ ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ግምት ያላቸውን የላብራቶሪ መሳሪያዎች ለክልሎች አስረክበዋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የጤና ምርመራ አገልግሎቶችን ለማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራትን በስፋት እያካሔደ ነው።

በዚህም በክልሎች በላብራቶሪ የሚሰጡ የጤና አገልግሎቶችን በቁሳቁስና በሰው ሃይል እንዲሟሉ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በድጋፍ የተሰጡት የላብራቶሪ መሳሪያዎች በአገሪቱ የሚሰጠውን የጤና አገልግሎት ጥራት ለማሳደግ እንደሚረዱ ተናግረዋል፡፡

በተለይም የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ የምርመራ አቅምን ለማጠናከር ከአለም ባንክ ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለክልሎች በድጋፍ የተሰጡት የጤና አገልግሎትን ለማሳደግ የሚያስችሉ የምርመራ መሳሪያዎች ከአለም ባንክ በድጋፍ የተገኙ መሆኑን አመልክተዋል።

ድጋፉ ከዚህ ቀደም ወደ ውጭ ተልከው ምርመራ የሚደረግባቸውን የጤና አገልግሎቶች በሀገር ውስጥ ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ሀይሉ በበኩላቸው፥ መንግስት የጤና ምርመራ ላብራቶሪዎችን አቅም በመገንባት የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጡ እያደረገ ነው ብለዋል።

የተደረገው ድጋፍ ጥራቱን የጠበቀ የጤና ምርመራ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል እንደሆነም ነው የገለጹት።

ኢንስቲትዩቱም የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ለብሔራዊና ለክልል የጤና ላብራቶሪዎች ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

ከተደረገው ድጋፍ በተጨማሪ 55 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ የሞተር ብስኪሌቶች ለክልል ጤና ተቋማት ተሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም