የፀጥታ መረጃ ስርዓትን በማጠናከር ለዜጎች ሁለንተናዊ ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ በጋራ መስራት ይገባል- ሚኒስቴሩ - ኢዜአ አማርኛ
የፀጥታ መረጃ ስርዓትን በማጠናከር ለዜጎች ሁለንተናዊ ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ በጋራ መስራት ይገባል- ሚኒስቴሩ
ሆሳዕና፤ ታኅሣሥ 25/2017(ኢዜአ)፦ በሀገሪቱ የፀጥታ መረጃ ስርዓትን በማጠናከር ለዜጎች ሁለንተናዊ ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ በቅንጅት መስራት እንደሚገባ የሰላም ሚኒስቴር ገለጸ።
የሰላም ሚኒስቴር ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ጋር በመተባበር በፀጥታ መረጃ ዘርፍ፣ በግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያና ፈጣን ምላሽ ምንነት ዙሪያ ለክልሉ የጸጥታ ዘርፍ ባለሙያዎች በሆሳዕና ከተማ ስልጠናን ሰጥቷል።
በሚኒስቴሩ የግጭት አስተዳደር ዘርፍ የሁኔታ መከታተያ የስራ ሂደት ባለሙያ አቶ ታደሰ ሜጋ እንደገለፁት፤ በሀገሪቱ የጸጥታ መረጃ ስርዓትን በማጠናከር ለዜጎች ሁለንተናዊ ሰላምና ደህንነት መረጋገጥ በትብብር መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።
በፀጥታ መረጃ፣ በግጭት አስተዳደርና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ፈጣን ምላሽ ዘርፍን ማጠናከርና የሰው ኃይል ማብቃት ላይ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ሊከሰት የሚችልን ግጭት አስቀድሞ በማወቅ ማምከንና መከላከል የሚቻልበት ምህዳር መፍጠርና ሰላምን ማጽናት ላይ በጋራ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል ።
የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ኃይሉ ማቴዎስ በበኩላቸው መረጃ ለጸጥታ ስራ ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።
ወቅታዊ ሁኔታን ታሳቢ ያደረገ የፀጥታና የህዝብ ደህንነትና የግጭት አመላካች መረጃዎችን መሰብሰብ፣ መተንተን፣ ማስተዳደር እና ጥቅም ላይ ማዋል ላይ በተደረገ ጥረት ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል።
ለሁለት ቀናት በቆየው ስልጠና የክልሉ ሁሉም መዋቅሮች የጸጥታ ዘርፍ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።