ቀጥታ፡

በክልሉ እየተከናወነ ያለውን የግብርና ናሙና ቆጠራ በባለቤትነት በመደገፍ ለውጤታማነቱ እንሰራለን - ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ

አፋር፤ ታህሳስ 25/2017(ኢዜአ)፦በአፋር ክልል እየተካሄደ ያለውን የግብርና ናሙና ቆጠራ በባለቤትነት በመደገፍ ለውጤታማነቱ እንደሚሰሩ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት የስራ ኃላፊዎች ከአፋር ክልል፣ የዞንና የወረዳ የስራ ኃላፊዎች ጋር የግብርና ቆጠራን በጥራትና በፍጥነት ማከናወን በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ዛሬ ተወያይተዋል ።


 

በውይይቱ ላይ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድሩ እንደገለፁት፤ የግብርና ናሙና ቆጠራው ለአርብቶ አደሩ ወሳኝ እንደመሆኑ ለስኬቱም ህብረተሰቡን በማስገንዘብ የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ስታስቲክስ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር በከር ሻሌ(ዶ/ር) በበኩላቸው ከ22 ዓመታት በኋላ እየተካሄደ ያለው የግብርና ናሙና ቆጠራ እንደ አገር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።

ቆጠራው አርብቶ አደሩ ካለው ከፍተኛ የእንስሳት ሃብት በተጨማሪ በግብርናው ልማት ረገድ ያለውን እምቅ አቅም እውን ለማድረግና በኢኮኖሚው ውስጥ በሚፈለገው ልክ እንዲካተት አዳዲስ ዕድሎችን እንደሚፈጥር ተናግረዋል።

በአፋር ክልል የተጀመረው የግብርና ናሙና ቆጠራ የተሳካ እንዲሆን አመራሩ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል።

የአፋር ክልል ፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሐሚድ ዱላ በበኩላቸው ''ይህ ቆጠራ ለህብረተሰባችን እንደ ዕድል ጭምር የሚቆጠር በመሆኑ በታማኝነት ማከናወን እንዲቻል በትብብር ይሰራል'' ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም