ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የምታደርገው ጥረት ውጤት አስመዝግቧል - አቶ ስዩም መኮንን

አዲስ አበባ፤ታኅሣሥ 25/2017(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት የምታደርገው ጥረት ውጤት ማስመዝገቡን የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን ገለጹ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ካርቦን ገበያ ሽያጭ ስትራቴጂ አውደ ጥናት የምክክር መድረክ በአዲስ አበባ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ቅጥር ግቢ ተካሂዷል። 

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ስዩም መኮንን በበይነ መረብ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ኢኮኖሚ ለመገንባት ሰፋፊ ተግባራትን እያከናወነች አንደምትገኝ ገልጸዋል። 

በአረንጓዴ አሻራ፣ በታዳሽ የኃይል አማራጭ፣ በግብርና ምርታማነትና በቆሻሻ አወጋገድ የምታካሂደው ልማት ሙቀት አማቂ ጋዞችን በመቀነስ ስኬት እያስመዘገበች ነው ብለዋል።

በቀጣይም ብሔራዊ የካርቦን ገበያ ሽያጭ ስትራቴጂን በመተግበር ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል። 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የካርቦን ገበያ ሽያጭ ስትራቴጂም የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በማሳለጥ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ትብብርን ለማዳበር እንደሚያግዝ አንስተዋል።


 

በመንግስታቱ ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፍ ስምምነት ገበያና ገበያ ነክ ያልሆኑ ማላመድ ክፍል ቡድን መሪ ፍሊፕ ኢሬ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ካርቦን ገበያ ሽያጭ ስትራቴጂ በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ያላትን ሚና ለማሳደግ ጉልህ ፋይዳ ይኖረዋል ብለዋል።

የመንግስታቱ ድርጅትም ኢትዮጵያ አየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን ለመከላከል በምታደርገው ጥረት ትብብሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

በፕላንና ልማት ሚኒስቴር የአካበቢና የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ስትራቴጂክ አጋርነት መሪ ሥራ አስፈፃሚ መንሡር ደሴ፤ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ የምትመራበት የካርበን ገበያ ሽያጭ ስትራቴጂ አልነበራትም ብለዋል።


 

ብሔራዊ የካርቦን ገበያ ሽያጭ ስትራቴጂ መዘጋጀቱም በደን ልማት፣ በትራንስፖርት፣ በቆሻሻ አወጋገድና በኃይል አማራጭ ልማት ላይ በምታበረክተው ልክ ተጠቃሚ የሚደርጋት መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም ሙቀት አማቂ ጋዞችን በመቀነስ፣ አረንጓዴ ኢኮኖሚ በማሳለጥና የዜጎችን ተጠቃሚነት በማሳደግ የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ስራን ለማገዝ ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው አስረድተዋል።

በፕላንና ልማት ሚኒስቴር የካርቦን ገበያ ሽያጭ ቡድን መሪ የሺወርቅ አሰፋ፤ የአየር ንብረት ለውጥ ስራ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት በትብብር የሚሰሩት ተግባር ነው ብለዋል።


 

በዝግጅት ሂደት ላይ የሚገኘው የብሔራዊ ካርቦን ሽያጭ ስትራቴጂ ተግባራዊ ሲሆን የኢትዮጵያን ጸጋ በመለየት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንደሚያመጣ ገልጸዋል። 

በዚህም የብሔራዊ ካርቦን ገበያ ስትራቴጂው የኢትዮጵያን የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል አበርክቶ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲገነዘብ የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።

በብሔራዊ የካርቦን ገበያ ሽያጭ ስትራቴጂ አውደ ጥናት የምክክር መድረክ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር፣ የዓለም አቀፍ አጋር ተቋማትና የሀገራት ኤምባሲ የስራ ኃላፊዎች እና ተወካዮች ተገኝተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም