ደንበኞች በዲጂታል አማራጮች የበዓል ግብይት እንዲፈጽሙ የሚያስችል በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን ባንኮች አስታወቁ - ኢዜአ አማርኛ
ደንበኞች በዲጂታል አማራጮች የበዓል ግብይት እንዲፈጽሙ የሚያስችል በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን ባንኮች አስታወቁ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 25/2017(ኢዜአ)፡-ደንበኞች ወደ ቅርንጫፍ ባንኮች መምጣት ሳይጠበቅባቸው በፈለጉት ቦታ ሆነው በዲጂታል አማራጮች የበዓል ግብይት እንዲፈጽሙ የሚያስችል በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን ባንኮች ገለፁ።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መጪዎቹን የገናና ጥምቀት በዓላት በማስመልከት በሽያጭ መፈፀሚያ (ፖስ) ማሽን ከአንድ ሺህ ብር በላይ ግብይት ለሚፈፅሙ ደንበኞቹ በዕጣ የ 10 ሺህ ብር ሽልማት ማዘጋጀቱን ተናግሯል።
በበዓላት ወቅት የፍጆታ እቃዎች ለመሸመት ጥሬ ገንዘብ ይዞ መገበያየት የተለመደ ሲሆን ይህም ሸማቹን ለስርቆት ሊዳርግ ይችላል ።
ይህንኑ ለመከላከልና ህብረተሰቡ ሳይጉላላ የተቀላጠፈ የግብይት አገልግሎት እንዲያከናውን ባንኮች የተለያዩ የዲጂታል ግብይት አማራጮችን ማዘጋጀታቸውን ለኢዜአ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል ባንኪንግ ዲቪዥን መርቻንትና ኤጀንት ማኔጅመንት ዳይሬክተር ብሌን ኃይለሚካኤል ለኢዜአ እንደገለጹት የዲጂታል ባንኪንግ ደንበኞች ባሉበት ሆነው እንዲገለገሉ የሚያስችል ነው።
ባንኩ በተለያዩ አማራጮች የዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎቶችን እያቀረበ መሆኑን ገልፀው አገልግሎቱ የደንበኞችን ጊዜ የሚቆጥብና በቀላሉ ክፍያን መፈፀም የሚያስችል ነው ብለዋል።
ከታህሳስ 21 እስከ ጥር 27 ድረስ በፖስ ማሽን ከ 1 ሺህ ብር በላይ ግብይት ለሚፈፅሙ ደንበኞቹ በየሶስት ቀኑ ዕጣ በማውጣት የ10 ሺህ ብር ዋሌት ካርድ እንደሚሸልም ተናግረዋል።
የዕጣ አሸናፊዎች ስም ዝርዝር በባንኩ ማህበራዊ ድረ-ገፆች እንደሚገለፅም ነው ያስረዱት።
ደንበኞች የተለያዩ የዲጂታል አማራጮችን በመጠቀም የበዓል ግብይት በመፈፀም ጊዜያቸውን እንዲቆጥቡ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በእናት ባንክ ዲጂታል ባንኪንግ ከፍተኛ ባለሙያ ቃልኪዳን አስራት በበኩላቸው ባንካቸው ለደንበኞቹ በተለያዩ የዲጂታል አማራጮች ቀልጣፋ የሆነ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በበዓል ግብይትም ደንበኞች ወደ ቅርንጫፍ መምጣት ሳይጠበቅባቸውና የገንዘብ ኖቶችን ሳይዙ ግብይት መፈፀም እንዲችሉ የዲጂታል ባንኪንግ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ነው ያስታወቁት።