ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ያላትን ሚና አጠናክራ ትቀጥላለች - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 25/2017(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ያላትን ሚና አጠናክራ እንደምትቀጥል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ገለጹ፡፡

አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በወቅታዊ የዲፕሎማሲና የውጭ ግንኙነት ዙሪያ ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን የጎላ አበርክቶ እያደረገች መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሱዳናውያን ችግራቸውን በራሳቸው በመፍታት ወደ ቀደመ ሰላማቸው እንዲመለሱ እየሰራች መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በቀጣናው ሽብርተኝነትን በመከላከል ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ኢትዮጵያ ያላትን ሚና አጠናክራ ትቀጥላለች ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከድህረ አትሚስ በኋላ በሶማሊያ የሚኖረው የሀይል ስምሪት ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ እንዲከናወን ትፈልጋለች ያሉት አምባሳደር ነብያት፤ ከአንካራው ስምምነት በኋላ ውይይቶች መቀጠላቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ባለፈው ሳምንት በሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አሊ ኦማር የተመራ የሶማሊያ ልዑክ በኢትዮጵያ የስራ ጉብኝት በማድረግ አልሸባብን በጋራ በመዋጋትና በቀጣናዊ ትብብር ዙሪያ ውጤታማ ውይይት መደረጉን አስታውሰዋል።

ትናንት ደግሞ በኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ የተመራ የኢትዮጵያ ልዑክ በሞቃዲሾ ፍሬያማ ውይይት ማድረጉን አስታውቀዋል።

በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የድጋፍና ማረጋጋት ተልዕኮ(AUSSOM) ስኬታማ በሚሆንባቸው ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን ገልጸው፤ በቀጣይም የሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች በአዲስ አበባ እንደሚመክሩ ይጠበቃል ብለዋል።

በተጨማሪም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) የኢትዮጵያ ቁልፍ አጋር በሆነችው ጅቡቲ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

በጉብኝታቸውም ከጅቡቲ ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጌሌ እና ከሌሎች ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች ጋር በሁለቱ ሀገራት የጋራ ጥቅምና በቀጣናው ሰላምና ልማት ላይ መወያየታቸውን ገልጸዋል።

አልሸባብን በጋራ መከላከል፣ የነዳጅ መስመር ማስፋፋት፣ ቀጣናዊ ትስስር እና ሌሎች የጋራ ጉዳዮች ላይ ትብብራቸውን ለማጠናከር መስማማታቸውንም አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ በ38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያስጠብቁ ውጤቶችን ማስመዝገብና የሀገር ገጽታን ማስተዋወቅ የሚያስችሉ ዝግጅቶች እያደረገች መሆኑን ገልጸዋል።

ለዚህም የኢትዮጵያን ገጽታ ማስተዋወቅ የሚያስችሉ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶችን በማሰልጠን እንግዶቿን እየተጠባበቀች መሆኑን ነው አምባሳደር ነብያት ጌታቸው በመግለጫቸው ያመላከቱት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም