ቀጥታ፡

የተሻሻለ የቡና ዝርያን በማልማት ጥሩ ምርት እያገኘን ነው - የምዕራብ ጉጂ ዞን አርሶ አደሮች

ነገሌ፤ ታህሳስ 25/2017(ኢዜአ)፡- የተሻሻለ የቡና ዝርያን በማልማት ጥሩ ምርት እያገኙ መሆኑን የምዕራብ ጉጂ ዞን አርሶ አደሮች ገለጹ፡፡

አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ አርሶ አደሮች አቶ ንጋቱ ሂርባዬ፣ ከ10 አመታት በላይ ቡናን የማልት ልምድ ያላቸው ሲሆን ቀደም ሲል የአካባቢ ዘርን ተጠቅመው ከሄክታር ከ6 እና 8 ኩንታል ያገኙ ነበር፡፡


 

ዘንድሮ የተሻሻለ የቡና ዝርያ አልምተው እስካሁን ከአንድ ሄክታር መሬት ብቻ 24 ኩንታል ድፍን ቡና ምርት ሲሰበስቡ ከቀሪ 4 ሄክታር መሬታቸውም ከአንድ መቶ ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠብቁ ገልጸዋል፡፡


 

ሌላው አርሶ አደር መልካ ሂርባዬ ከሶስት አመት በፊት በ5 ሄክታር መሬት ላይ ያለሙት የቡና ችግኝ ዘንድሮ አብዛኛው ለምርት በመድረሱ ከ50 ኩንታል በላይ አጠቃላይ ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡


 

አርሶ አደር ቦጋለች ፈይሳ በበኩላቸው በተሻሻለ ቡና ልማት ከሸፈኑት 25 ሄክታር መሬት ጥሩ ምርት እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።


 

የምዕራብ ጉጂ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ሀላፊ አቶ አያኖ አለማየሁ፣ በዞኑ ከ149 ሺህ 250 ሄክታር የሚበልጥ መሬት አካባቢና በተሻሻለ የቡና ዝርያ እየለማ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

ከዚህ ውስጥ ከ59 ሺህ ሄክታር የሚበልጠው መሬት በተሻሻለ 11 አይነት የቡና ዝርያ መሸፈኑን ገልጸዋል፡፡

በዞኑ ከለማው ቡና ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቁ ገልጸው በእስካሁኑም 6 ወረዳዎች 35 ሺህ ኩንታል በላይ የቡና ምርት መሰብሰቡን አስታውቀዋል፡፡


 

የተሻሻሉት የቡና ዝርያዎች ከጅማና ከሌሎች ግብርና ምርመር ማዕከላት የወጡና በአጭር ጊዜ የሚደርሱ እንዲሁም በሽታን በመቋቋም ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ ናቸው ብለዋል፡፡

የተሻሻሉት የቡና ዝርያዎች ነባሩ የቡና ዝርያ ምርት ለመስጠት የሚወስድበትን ከ5 እስከ 7 አመታት ወደ 3 ዓመት የሚያሳጥሩ ምርቱንም በእጥፍ የሚያሳድጉ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

በዞኑ 6 ወረዳዎች ከ134 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች በቡና ልማት እየተሳተፉ መሆናቸውን ከምክትል ሀላፊው ገለጻ መረዳት ተችሏል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም