በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የመኸር ሰብል መሰብሰቡን ተከትሎ የገበያው ዋጋ መረጋጋት እያሳየ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የመኸር ሰብል መሰብሰቡን ተከትሎ የገበያው ዋጋ መረጋጋት እያሳየ ነው
ደብረ ብርሃን፤ ታህሳስ 25/2017(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የመኸር ሰብል መሰብሰቡን ተከትሎ የገበያው ዋጋ መረጋጋት እያሳየ መሆኑን የዞኑ ንግድና ገበያ ልማት መመሪያ ገለጸ።
የመመሪያው ኃላፊ አቶ ዘውገ ንጉሴ እንደገለፁት፤ አርሶ አደሩ በየአካባቢው ባሉ የግብይት ማዕከላት ያመረተውን በመሸጥና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በመግዛት ገበያው እንዲረጋጋ አስተዋጽኦ እያደረገ ነው።
በተጨማሪም የገበያ ዋጋን ለማረጋጋት ከ41 የሸማች ህብረት ስራ ማህበራት ጋር ትስስር መፍጠር መቻሉንም ገልፀዋል።
ባለፉት አምስት ወራት ከ172 ሚሊዮን ብር በላይ በመመደብ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ስኳር፣ መኮሮኒን ጨምሮ ሌሎች ምርቶችን ለተጠቃሚዎች ማቅረብ ተችሏል ብለዋል።
ለመጪው የገና በዓልም የእርድ እንስሳት፣ ሽንኩርት፣ ቅቤና ሌሎች ምርቶች በስፋት እንዲቀርቡ እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ህብረት ስራ ማህበራት ማደራጃና ማስፋፊያ ተጠሪ ጽህፈት ቤት የግብይት ቡድን መሪ አቶ ተክሌ ሙሉነህ የገበያ ዋጋን ለማረጋጋት ዩኒኖችና ማህበራት 122ሺህ 126 ኩንታል ሰብል ግዥ ፈፅመዋል ብለዋል።
በተለይም የበዓል ገበያ አቅርቦትን ታሳቢ ያደረገ ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ ለተጠቃሚዎች እንዲቀርብ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
የዞኑ ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ሰለሞን ቀለሙ በበኩላቸው፤ በ2016/17 የምርት ዘመን 549 ሺህ 601 ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች ማልማት ተችሏል።
ከለማው መሬትም 16 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል ምርት የቅድመ ምርት ትንበያ መደረጉን ጠቅሰው እስካሁን ባለውም ከ8 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን ገልፀዋል።
የምርቱ እድገት ለኢንዱስትሪው ግብዓት ከማቅረብ ባለፈ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ለገበያ መረጋጋት ተጨማሪ እድል እንደሚፈጥር አስረድተዋል።