ዩኒቨርሲቲው የመከላከያን ክብር በልህቀት በማረጋገጥ ከኢትዮጵያ አልፎ በአፍሪካ ተጽእኖ ፈጣሪ ተቋም ለመሆን እየሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 25/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ የመከላከያን ክብር በልህቀት በማረጋገጥ ከኢትዮጵያ አልፎ በአፍሪካ ተጽእኖ ፈጣሪ ተቋም ለመሆን እየሰራ እንደሚገኝ የዩኒቨርሲቲው ኮማንዳንት ብርጋዲየር ጀኔራል ከበደ ረጋሣ ገለጹ።

የኢትዮ ቴሌኮም አመራሮች የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲን ጎብኝተዋል።

አመራሮቹ በዩኒቨርሲቲው እየተሰጡ የሚገኙ የትምህርት ፕሮግራሞች፣ የጥናትና የምርምር ውጤቶች፣ የአይሲቲ መሰረተ ልማቶችና ሌሎች ስራዎችን ተመልክተዋል።


 

የዩኒቨርሲቲው ኮማንዳንት ብርጋዲየር ጀኔራል ከበደ ረጋሣ ዩኒቨርሲቲው ኢትዮጵያን ሌትና ቀን በጀግንነት እየጠበቀ የሚገኘው የሀገር መከላከያ ሰራዊትን በቴክኖሎጂ እውቀት የበቃና የዘመነ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው የመከላከያን ክብር በልህቀት ማረጋገጥ በሚያስችል አግባብ በትምህርትና በምርምር የተሻለ ሆኖ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ሽግግርን ተደራሽ ማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

ከኢትዮጵያ አልፎ በአፍሪካ ላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ ተቋም ለመሆን እየሰራ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

ኢትዮ ቴሌኮምን ጨምሮ ሌሎች ተቋማት የዩኒቨርሲቲውን የለውጥ ሂደትና ሙያተኞችን በእውቀትና በክህሎት ብቁ ለማድረግ እየተከናወነ ላለው ስራ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።


 

የኢትዮ ቴሌኮም ቺፍ ቴክኖሎጂ ኦፊሰር አቶ ታሪኩ ደምሴ ተቋሙ የዩኒቨርሲቲውን የለውጥ ሂደት እና የመከላከያን የእውቅትና ቴክኖሎጂ አቅም የሚያሳድጉ ድጋፎችን እንደሚያደርግ አመልክተዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም ከዩኒቨርሲቲው ጋር ልምድና እውቀትን ማጋራት ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች በትብብር እንደሚሰራ መግለጻቸውን ከመከላከያ ሰራዊት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም