ቀጥታ፡

የፕሪሚየር ሊጉ 12ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ከዛሬ ጀምሮ ይካሄዳል

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 25/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ12 ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ይጀመራል።

ፕሪሚየር ሊጉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአፍሪካ ሀገራት ዋንጫ (ቻን) ከሱዳን ጋር በነበረው የማጣሪያ ጨዋታ ምክንያት ከታህሳስ 2 ቀን 2017 ዓ.ም እንስቶ ተቋርጦ ነበር።

ሊጉ ዛሬ ወደ ውድድር ሲመለስ ሁለት ጨዋታዎች በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይካሄዳሉ።

አርባምንጭ ከተማ ከሲዳማ ቡና ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

በበረከት ደሙ የሚመራው አርባምንጭ ከተማ በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ ሶስት ጊዜ ተሸንፏል። በጨዋታዎቹ አራት ግቦችን ሲያስቆጥር ስድስት ግቦችን አስተናግዷል።

ቡድኑ በ13 ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ተጋጣሚው ሲዳማ ቡና ባለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም። አራት ጊዜ ሲሸነፍ 1 ጊዜ አቻ ወጥቷል።

በአምስቱ ጨዋታዎች ሶስት ጎሎችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ ዘጠኝ ግቦችን አስተናግዷል። በዘላለም ሽፈራው የሚመራው ሲዳማ ቡና በ13 ነጥብ ተጋጣሚውን በግብ ክፍያ በልጦ 10ኛ ደረጃን ይዟል።

የ12ኛ ሳምንት ሁለተኛ ጨዋታ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ፋሲል ከነማ እና ሃዋሳ ከተማን ያገናኛል።

ፋሲል ከነማ በሊጉ ካደረጋቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች መካከል ሁለቱን ሲያሸንፍ በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ ተሸንፏል፤ አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል።

ቡድኑ በጨዋታዎቹ አምስት ግቦችን ሲያስቆጥር በተመሳሳይ አምስት ጎሎችን አስተናግዷል። በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው ፋሲል ከነማ በ14 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ሃዋሳ ከተማ ባለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ድል አላስመዘገበም። ሶስት ጊዜ ሲሸነፍ ሁለት ጊዜ ደግሞ ነጥብ ተጋርቷል። በአምስቱ ጨዋታዎች ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር አምስት ግቦችን አስተናግዷል።

በጊዜያዊ አሰልጣኞቹ ወንድማገኝ ተሾመ እና ብርሃኑ ወርቁ የሚመራው ሃዋሳ ከተማ በዘጠኝ  ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

ክለቡ ከዋና አሰልጣኙ ዘርዓይ ሙሉ ጋር መለያየቱ ይታወቃል።

የሊጉ መርሃ ግብር ነገም ቀጥሎ ሲውል ባህር ዳር ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ወላይታ ድቻ እና ኢትዮጵያ ቡና የ12ኛ ሳምንት አራፊ ቡድኖች ናቸው።

የ12ኛ ሳምንት መርሃ ግብር እስከ ታህሳስ 28 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚቆይ የሊጉ አክሲዮን ማህበር መረጃ ያመለክታል።

መቻል በ21 ነጥብ ሊጉን እየመራ ይገኛል።

የድሬዳዋ ከተማው መሐመድ ኑር ናስር እና የኢትዮጵያ ቡናው አንተነህ ተፈራ በስድስት ግቦች የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት እየመሩ ነው።

ዩጋንዳዊው የድሬዳዋ ከተማ አጥቂ ቻርልስ ሙሲጌ፣ የመቻሉ ሽመልስ በቀለ እና የመቀሌ 70 እንደርታው ያሬድ ብርሃኑ በተመሳሳይ አምስት ግቦች ይከተላሉ።

ከ12ኛ እስከ 19ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም እንደሚካሄድ ማህበሩ አስታውቋል።

ከ1ኛ እስከ 11ኛ ሳምንት መርሃ ግብር በድሬዳዋ ስታዲየም መደረጉ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም