ሙዝየሙ ተፈጥሯዊ ሀብቶቻችንን አውቀን፤ ዕሴት ጨምረን ወደ ሀብትነት የመቀየር ጉዟችን አንድ ማሳያ ነው- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
ሙዝየሙ ተፈጥሯዊ ሀብቶቻችንን አውቀን፤ ዕሴት ጨምረን ወደ ሀብትነት የመቀየር ጉዟችን አንድ ማሳያ ነው- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ታኅሣሥ 25/2017 (ኢዜአ)፦ የፓላስ ሙዝየም ተፈጥሯዊ ሀብቶቻችንን አውቀን፤ ዕሴት ጨምረን ወደ ሀብትነት የመቀየር ጉዟችን አንድ ማሳያ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ታሪክ መማረሪያ ሳይሆን መማሪያ፤ የክት ሳይሆን የአዘቦት መሆን አለበት ሲሉ ተናግረዋል።
ዛሬ ከምሁራን፣ ከኪነ ጥበብ፣ ከንግዱ ማኅበረሰብ አባላት እና ከታዋቂ ሰዎች ጋር ታሪካዊ ዕሴቱን ጠብቆ በታደሰው ብሔራዊ ቤተ መንግሥት መገኘታቸውን ገልጸዋል።
ይህ ሙዝየም ሕዝብ የሀብቱ የሩቅ ተመልካች ሳይሆን ተጠቃሚ መሆን አለበት በሚል መርሕ ተፈጥሯዊ ሀብቶቻችንን አውቀን፤ ዕሴት ጨምረን ወደ ሀብትነት የመቀየር ጉዟችን አንድ ማሳያ ነው ብለዋል።
የታሪክና የቅርስ ምሁራን ደግሞ ታሪካችን እና ቅርሳችን ለሕዝቦች መቀራረብና መተሣሠር እንዲጠቅም ማድረግ እንደሚኖርባቸው አመልክተዋል።
አሳዛኝና አስቀያሚ ታሪክ የሌለው ሀገር የለም ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ጉልበት፣ ጊዜና ገንዘባችንን ማዋል ያለብን ደግሞ ሕዝብን የሚያቀራርቡ፣ የሚያኮሩ እና የሚያስተሣሥሩ ታሪኮቻችን ላይ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
የኪነ ጥበብ ባለሞያዎችም ይሄ ሙዝየም የድርሰታችሁ፣ የግጥማችሁ፣ የፊልማችሁ፣ የዜማችሁ ማዕከል እንደሚሆን አምናለሁ ነው ያሉት።
ፊልሞቻችሁና፣ ሙዚቃዎቻችሁ፤ ድርሰቶቻቸሁና ቅኔዎቻቸሁ ደግሞ እነዚህን የኢትዮጵያ ከፍታ ማሳያ ሥፍራዎች እንዲዳስሱ አደራ ለማለት እፈልጋለሁ ብለዋል።
የንግዱ ማኅበረሰብ አባላት ቅርሶቻችንንና ታሪካዊ ቦታዎቻችንን ስናለማ እያደረጋችሁ ላላችሁት እገዛ እያመሰገንሁ ይሄ እገዛችሁ እንዲቀጥል አደራ እላለሁ ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።