በመከላከያ ሚኒስትሯ አይሻ መሀመድ (ኢ/ር) የተመራ የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን በሶማሊያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በመከላከያ ሚኒስትሯ አይሻ መሀመድ (ኢ/ር) የተመራ የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን በሶማሊያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አደረገ
አዲስ አበባ፤ ታኅሳሥ 25/2017 (ኢዜአ):- በኢ.ፌ.ዲ.ሪ. መከላከያ ሚኒስትር አይሻ መሀመድ (ኢ/ር) የተመራ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ያሉበት የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በሶማሊያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት አድርጓል።
የልዑካን ቡድኑ ከሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼኽ ማህሙድ ጋር ውጤታማ ውይይት ያደረገ ሲሆን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ለፕሬዝዳንቱ የተላከ መልዕክት አድርሰዋል።
በውይይቱ ወቅት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ሶማሊያን ጨምሮ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋትን ለማረጋገጥ በጋራ ለመስራት ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የAUSSOM ተልዕኮ ውጤታማ ለማድረግ በትብብር ለመስራት የተስማሙ ሲሆን የሁለትዮሽ ትብብራቸውንም ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ የጉብኝት ልውውጦች ለማጠናከርና በቅርቡ የሶማሊያ ከፍተኛ ኃላፊዎች በአዲስ አበባ ጉብኝት በማድረግ ውይይት ለማካሄድ ተስማምተዋል።
የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስትር አብድርቋድር ኑር ጃማ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሶማሊያን ሰላም ለማረጋገጥ ለከፈለው መስዋዕትነት እና ላበረከተው አስተዋጽዖ ያላቸው አክብሮት እና ምስጋና ገልጸዋል።
የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. መከላከያ ሚኒሰትር አይሻ መሀመድ (ኢ/ር) በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ሰላም እና መረጋጋት የበኩሏን አስተዋጽኦ ለማበርከት ቁርጠኛ ነች።
ሽብርተኝነትን መዋጋት የሁለቱ አገራት ቁልፍ የትብብር ማዕከል መሆን እንደሚገባው ሚኒስትሯ አስምረውበታል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በበኩላቸው የሶማሊያ ሰላም ማለት የኢትዮጵያ ሰላም መሆኑን ገልጸው፤ በቀጣናው የሚስተዋለው የጸጥታ ችግር አገራቱ የልማት አጀናዳዎቻቸው ላይ እንዳያተኩሩ እያደረገ መሆኑን አንስተዋል።
አምባሳደር ምስጋኑ ሁለቱ አገራት ትብብራቸውን በማጠናከር ከጸጥታ ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ችግሮችን በፍጥነት በመቅረፍ ሙሉ ትኩረትን ልማት ላይ ማደረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ባለፈው ሳምንት በሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አሊ ሞሀመድ ኦማር የተመራ የሶማሊያ ልዑካን ቡድን በኢትዮጵያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት በማድረግ ከሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ጋር ውይይት ማድረጉ ይታወሳል።