የቅዳሜና ዕሁድ ገበያዎች ለገበያ መረጋጋት እያገዙ ነው - ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 24/2017(ኢዜአ)፦በቅዳሜና እሁድ ገበያዎች የሚቀርቡ የተለያዩ ምርቶች ለገበያ መረጋጋት የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር አባይ ገለጹ።

ለገበያ መረጋጋት የተሻለ አበርክቶ ላደረጉ አምራቾችና አቅራቢዎች የፌዴራልና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት የዕውቅና መርሀግብርና ውይይት ተካሂዷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፥ የቅዳሚና እሁድ ገበያ የምርት አቅርቦት ሳይቆራረጥ በማቅረብ ለዋጋ መረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡

በቀጣይም የከተማውን ዕድገት ታሳቢ ባደረገ መልኩ ዘመናዊ አድርጎ ለማደራጀት አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግ ገልጸው፤ አምራችና አቅራቢውን በማስተሳሰር የዋጋ ማረጋጋት ስራው በትኩረት እንደሚሰራም ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ኃላፊ ሀቢባ ሲራጅ በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት "ምርት አቅርቦት ለገበያ ማረጋጋት'' በሚል መሪ ሀሳብ የተለያዩ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

በዚህም ምርትን ከአምራቹ ወደ ሸማቹ በቀጥታ ለማቅረብ ጥረት መደረጉን አስታውሰዋል።

ለአብነትም በግብርና ምርቶች መሸጫ ማዕከላት፣በቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ምርት በማቅረብ ለገበያ መረጋጋት የተለያዩ አምራቾችና አቅራቢዎች አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ በማቅረብ ረገድ የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ተናግረዋል።

በቀጣይም የተገኘው መልካም ተሞክሮ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለዋጋ መረጋጋት የጎላ አበርክቶ ላደረጉ አምራቾች፣አቅራቢዎችና ባለድርሻ አካላት ዕውቅና መሰጠቱን ገልጸዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ ከተሳተፉት መካከል የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ተወካይ አቶ መስጠፋ ተኩ በቅዳሜና እሁድ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ደረጃ በማሳደግ ለሸማቹ ለመቅረብ እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

የግብርና ምርት አቅራቢ አቶ አለማየሁ ረጋ በበኩላቸው የሚያመርቱትን ምርት በቀጥታ ለግብርና ምርት ማዕከላት በማቅረብ ላይ እንደሚገኙ ገልጸው፥ያገኙት ዕውቅና ጠንክረው በመስራት በዋጋ መረጋጋት ሂደት ይበልጥ እንዲተጉ እንደሚያነሳሳቸውን ተናግረዋል፡፡

የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች በ2014 በአምስት ስፍራዎች የተጀመረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት 197 መድረሳቸውን የቢሮው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም