በሚቀጥሉት አስር ቀናት በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች የበጋው ደረቅ፣ ፀሐያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ ተጠናክሮ ይቀጥላል - የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት - ኢዜአ አማርኛ
በሚቀጥሉት አስር ቀናት በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች የበጋው ደረቅ፣ ፀሐያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ ተጠናክሮ ይቀጥላል - የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 24/2017(ኢዜአ)፡- በሚቀጥሉት አስር ቀናት በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች የበጋው ደረቅ፣ ፀሐያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው የአየር ሁኔታ መግለጫ በጥቂት የደቡብ ምዕራብ፣ ሰሜን ምስራቅና መካከለኛ የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የተሻለ የደመና ሽፋን እንደሚኖራቸውም አስታውቋል።
በሚቀጥሉት ቀናት በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች የሚኖረው የበጋው ደረቅ የእርጥበት ሁኔታ የድህረ ሰብል ስብሰባ ተግባራትን ለማከናወን አመቺ እንደሚሆን እንደሚጠበቅ ገልጿል።
አርሶ አደሮች እና የሚመለከታቸው አካላት የሚኖረውን ምቹ የአየር ሁኔታ በመጠቀም ሰብልን ከማሳ የማንሳት፣ የማከማቸትና የመውቃት ተግባራትን ማከናወን እንደሚገባቸውም ኢንስቲትዩቱ አመላክቷል።
በደቡብ ምዕራብ፣ ምዕራብ፣ ሰሜን ምስራቅና መካከለኛው የሀገሪቱ ክፍሎች ላይ የሚኖረው አነስተኛ መጠን ያለው እርጥበት ለመጠጥ ውሃ አቅርቦት መሻሻል እና ለግጦሽ ሳር አውንታዊ ሚና ይኖረዋል ብሏል።
የበልግ ወቅትን ቀድመው ለሚጀምሩ አካባቢዎች ማሳን አስቀድሞ ከማዘጋጀት አንጻርም ጠቃሜታ እንዳለው ጠቁሟል።
ሁሉም የሀገሪቱ ተፋሰሶች በደረቅ የአየር ሁኔታ ስር የሚቆዩ ሲሆን ይህም ከትነት ጋር ተዳምሮ በግድቦች፣ በኩሬዎች፣ በወንዞችና በምንጮች ላይ መጠነኛ የውሃ መቀነስ ሊያስከትል ስለሚችል የውኃ ሀብትን በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል ነው ያለው ኢንስቲትዩቱ።