ቀጥታ፡

ወጣት ምቹ ጊዜ የሚጠብቅ ብቻ ሳይሆን ምቹ ጊዜን የሚፈጥር ነው - የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ፉአድ ገና

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 24/2017 (ኢዜአ)፥ወጣት ምቹ ጊዜ የሚጠብቅ ብቻ ሳይሆን ምቹ ጊዜን የሚፈጥር ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ፉአድ ገና ተናገሩ።

የትግራይ ክልል የወጣቶች ምክር ቤት የምስረታ ጉባኤ በመቀሌ ከተማ እየተካሄደ ነው።

አቶ ፉአድ ገና በምስረታ ጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ወጣት ምቹ ጊዜ የሚጠብቅ ብቻ ሳይሆን ምቹ ጊዜን የሚፈጥር በመሆኑ የወጣቱን ሁለንተናዊ ግንዛቤና አቅም የማሳደግ ስራ ልዩ ትኩረት እንደሚሻ ጠቁመዋል።


 

እየተደራጁ ያሉ የክልል ምክር ቤቶች የወጣቶች ድምጽ ሆነው ማገልገል እንዲችሉ በከፍተኛ ቁርጠኝነት እየተሰራ እንደሚገኝ አመላክተዋል።


 

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ሙና አህመድ በበኩላቸው፥ ወጣቶች ከተናጠል እንቅስቀሴ ይልቅ በጋራ ሲንቀሳቀሱ ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

መላ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ሁሉን አቀፍ በሆነ መልኩ ብቁና ተጽዕኖ ፈጣሪ ይሆኑ ዘንድ ጠንካራና ሁሉን አቀፍ የወጣት ምክር ቤቶች በሁሉም ክልሎችና ከተማ መስተዳደሮች በተዋረድ መቋቋም እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።


 

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት ጀነራል ጻድቃን ገብረትንሳይ፥ ለትግራይ ወጣቶች የተለያየ አይነት ጠንካራ አደረጃጀት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

በዚህ የክልሉ የወጣቶች ምክር ቤት መመስረቱ ለወጣቶች ብቻ ሳይሆን ለትግራይ ህዝብ ሁለንተናዊ ሰላም፤ልማትና እድገት ተስፋ ነው ብለዋል።


 

የትግራይ ክልል የወጣቶች ምክር ቤት 120 የጠቅላላ ጉባኤ አባላት ያሉት ሲሆን 11 ስራ አስፈጻሚና 5 ኦዲትና ቁጥጥር አባላትን ሰይሞ መመስረቱን ከኢትዮጵያ ወጣቶች ምክር ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም