ቀጥታ፡

የአትዮጵያ ንግድ ባንክ የደንበኞችን ፍላጎት መሰረት አድርጎ የሚሰጠውን አገልግሎት ይበልጥ ለማሳደግ እየሰራ ነው - አቶ አህመድ ሽዴ

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 24/2017(ኢዜአ)፡- የአትዮጵያ ንግድ ባንክ የደንበኞችን ፍላጎት መሰረት አድርጎ የሚሰጠውን አገልግሎት ይበልጥ ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ መሆኑን የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ "የላቀ አገልግሎት ደስተኛ ደንበኛ" በሚል መሪ ሀሳብ ከታህሳስ 24 እስከ ጥር 25 የሚቆይ የደንበኞች አገልግሎት ወር አስጀምሯል።


 

የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ፣ በመርኃግብሩ ማስጀመሪያ ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ እና የባንኩ ከፍተኛ አመራሮችና ሰራተኞች ተገኝተዋል።

በመርኃ-ግብሩ በባንኩ አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ከደንበኞች ጋር ውይይት፣ ለአንድ ሳምንት የሚቆይ አወደ ርዕይ እና ለደንበኞች ምስጋና የሚቀርብበት እንደሆነ ተመላክቷል።

የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አህመድ ሽዴ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት፤ ባንኩ ባለፉት 82 አመታት ላስመዘገባቸው ስኬቶች የደንበኞች አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው።

ደንበኞቹ ለባንኩ እምነት ሰጥተው አብረው በመስራታቸው ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ለባንኩ ደንበኞች ፍላጎት ምላሽ ለመስጠት አቅጣጫ በማስቀመጥ ተግባራዊነቱን እየተከታተለ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም ባንኩ የደንበኞችን ፍላጎት መሰረት በማድረግ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ይበልጥ ለማጠናከር በትኩረት እየሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

ባለፉት አመታት የደንበኞችን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ አዳዲስ አገልግሎቶች በማስጀመር ለደንበኞች ተደራሽ መደረጉንም ተናግረዋል።

የባንኩ የዳይሬክቶሮች ቦርድ የባንኩን አገልግሎት አሰጣጥ የላቀ ለማድረግም በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።


 

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ በበኩላቸው ባንኩ ከ45 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች እንዳሉት ገልጸዋል።

በመላ ሀገሪቱ የሚገኙት ደንበኞችም ለባንኩ እድገት እና ዘላቂነት ላበረከቱት አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርበው፤ በቀጣይም ባንኩ የደንበኞችን ፍላጎት መሰረት ያደረገ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም