ቀጥታ፡

ለኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ጥያቄ ላቀረቡ አገራት በሂደት ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ታህሳስ 24/2017(ኢዜአ)፦ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ለመሆን ጥያቄ ላቀረቡ አገራት በሂደት ምላሽ ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ገለጹ።

ከታዳሽ ምንጮች የኤሌክትሪክ ሃይል በማመንጨት ከአፍሪካ ከቀዳሚዎቹ ስፍራን የያዘችው ኢትዮጵያ በመሰረተ ልማቱም ይሆን ቀጣናውን ተጠቃሚ የማድረግ ጥረቷን ቀጥላለች።

ለዚህም የታዳሽ ኃይል አማራጭን በተለይም ከውሃ፣ ነፋስ፣ እንፋሎትና የጸሃይ ብርሃን የማምረት ስራዎች በስፋት በመከናወን ላይ ይገኛሉ።

በኃይል ስርጭትና ተደራሽነት ከምስራቅ አፍሪካ ባለፈ የአፍሪካ የኃይል ማዕከል ለመሆን ሰፊ ጥረት እየተደረገ መሆኑም ይታወቃል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ፤ በኃይል ልማትና ተደራሽነት እንዲሁም ቀጣናዊ ተጠቃሚነት ረገድ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

በእስካሁኑ ሂደት ከጎረቤት አገራት ሱዳን፣ ጅቡቲና ኬንያ ከኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታውሰው፥ በቅርቡ ለታንዛኒያ ለመሸጥ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ መጠናቀቁን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ከምታመነጨው አጠቃላይ የኤሌክትሪክ ሃይል 90 በመቶውን ለሀገር ውስጥ ፍጆታ በማዋል 10 በመቶውን ደግሞ ለተለያዩ አገራት እያቀረበች መሆኑን አንስተው፥ በቀጣይም የኃይል ልማትና ተደራሽነት ጥረቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያ በኩል ከኢትዮጵያ የኃይል ተጠቃሚነት ጥያቄ መቅረቡን ያስታወሱት ዋና ስራ አስፈጻሚው፥ ጥናት ተደርጎና የሃይል ማስተላለፊያ ጣቢያዎች ግንባታ ሲከናወን ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የኃይል ሽያጭ አገራትን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ምንጭ መሆኑን ጠቅሰው፥ የልማት ስራውና ቀጣናዊ የኃይል ትስስሩ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን የልማትና የኃይል አቅርቦት ፍላጎት ለማሳካት ሰፊ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፥ ለዘርፉ ልማት መሳካት የግሉ ባለሃብት ተሳትፎም እንዲታከልበት ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መረጃ እንደሚያሳየው በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሦስት ወራት ለጎረቤት ሀገራት ከቀረበ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ 31 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ገቢ መገኘቱ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም