ቀጥታ፡

ለበዓል ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ጥራትና ደህንነት ለማረጋገጥ ጠንካራ ቁጥጥር እየተደረገ ነው - ባለስልጣኑ

አዲስ አበባ፤ ታኅሣሥ 24/2017(ኢዜአ)፦ ከገና በዓልጋር ተያይዞ ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ጥራትና ደህንነት ለማረጋገጥ ጥብቅ ክትትልና ቁጥጥር እያደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ገለጸ፡፡

የገናን በዓል ጨምሮ በበዓላት ወቅት የፍጆታ ሸቀጦችና ምርቶች በከፍተኛ መጠን ለገበያ የሚቀርቡበትና ሰፊ ግብይት ይደረጋል።

በዚህም የበዓል ግብይት ወቅት የምርት ጥራትና ደህንነት መጓደል እንዳይከሰት የተቋማትን ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥርይሻል።

በጉዳዩ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው በኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣንን የምግብ ኢንስፔክሽን እና ህግ ማስፈጸም መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ሙላቱ ተስፋዬ እንደገለጹት፤ ለበዓል ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ጥራትና ደህንነት ለማረጋገጥ የተጠናከረ የክትትልና ቁጥጥር ስራ እየተከናወነ ይገኛል።

ሰፊ ግብይት በሚፈጸምባቸው አካባቢዎች በተለይም በምግብና ምግብ ነክ ምርቶች ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የጥራት ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ሸማቹ ህብረተሰብ በግብይት ወቅት የምርቶች ጥራትና የአገልግሎት ማብቂያ ጊዜን በጥንቃቄ አጣርቶ መሸመት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በግብይት ወቅት አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙ በባለስልጣኑ ነፃ የስልክ መስመር 8482 ማሳወቅ ወይም ለጸጥታ አካላት መረጃ መስጠት እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም