በስምጥ ሸለቆ የተከሰተውን ርዕደ መሬት ተከትሎ ከሳይንሳዊ ምልከታ ውጪ በሚሰራጩ መረጃዎች መደናገር አይገባም- አታላይ አየለ (ፕ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በስምጥ ሸለቆ የተከሰተውን ርዕደ መሬት ተከትሎ ከሳይንሳዊ ምልከታ ውጪ በሚሰራጩ መረጃዎች መደናገር አይገባም- አታላይ አየለ (ፕ/ር)
አዲስ አበባ፤ ታኅሣሥ 24/2017(ኢዜአ)፦ በአፋር ክልል የስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች የተከሰተውን ርዕደ መሬት ተከትሎ ከሳይንሳዊ ምልከታ ውጪ በሚሰራጩ መረጃዎች ዜጎች ሊደናገሩ እንደማይገባ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የዘርፉ ተመራማሪ ፕሮፌሰር አታላይ አየለ ገለጹ።
ርዕደ መሬት ወይም የመሬት መንቀጥቀጥ ከምድር በታች በሚገኙ ዓለታማ ቁሶች ግጭት የሚፈጠር እና ከስር ወደ ላይ በሚወጣ የታመቀ ሃይል ምክንያት የሚከሰት ተፈጥሯዊ ክስተት ስለመሆኑ የዘርፉ ተመራማሪዎች ይገልጻሉ።
ከአንድ ወር በፊት ጀምሮም በአፋር ክልል የስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች በተለይም በፈንታሌ ተራራና አካባቢው አልፎ አልፎ የመሬት መንቀጥቀጥ እየተከሰተ መሆኑ ይታወቃል።
ኢዜአ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦ ፊዝክስ ስፔስ ሳይንስና አስትሮኖሚ ተቋም የመሬት መንቀጥቀጥ ተማራማሪ እና መምህር ፕሮፌሰር አታላይ አየለን በጉዳዩ ዙሪያ አነጋግሯል።
በሳይንስ መሬት ሁልጊዜም በዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ላይ በመሆኗ እሳተ ገሞራ፣ መሬት መንሸራተትና መንቀጥቀጥና መሰል ተፈጥሯዊ አደጋዎች ተጠባቂ ክስተቶች ናቸው ይላሉ።
ፕሮፌሰሩ በአዋሽ ፈንታሌ ባሳለፍነው ዓመት መስከረም እና ጥቅምት ወር ላይ ተመሳሳይ የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተት እንደነበር አስታውሰው፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተደጋጋሚ እየተስተዋለ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች የሚከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ከቅልጥ ዓለት ጋር የተያያዘ መሆኑን ጠቅሰው ንዝረቱ የከፋ ጉዳት የሚያስከትል እንዳልሆነ ጠቁመዋል።
ከርዕደ መሬቱ ጋር ተያይዞ ሳይንሳዊ ምልከታ የሌላቸውና ዜጎችን የሚያሸብሩ የተሳሳቱ መረጃዎች እየተሰራጩ መሆኑን ጠቅሰው እውነታውን ከትክክለኛ የመረጃ ምንጭ ብቻ ማግኘት ይገባል ብለዋል።
በአዋሽ ፈንታሌና አካባቢው የተከሰተው ተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ ክስተትም የከፋ ጉዳት የማያስከትል መሆኑን ህብረተሰቡ መገንዘብ እንዳለበት ገልጸዋል።
በዘርፉ ላይ ግንዛቤን ማሳደግ እንዲሁም በመንግስት ደግሞ የባለሙያ ስልጠናን እና የሀገርን የኢኮኖሚ አቅም ታሳቢ ባደረገ መልኩ ለምርምር ስራ አጋዥ የሆኑ ቁሳቁሶችን ግዥ መፈጸም እንደሚገባም ተናግረዋል።