ቀጥታ፡

የጁገል ዓለም ዓቀፍ ቅርስ ጥበቃና እንክብካቤ ሥራ ተሞክሮ የሚወሰድበት ነው

ሐረር ታህሳስ 24/2017 (ኢዜአ):- የጁገል ዓለም ዓቀፍ ቅርስን የመጠበቅና የመንከባከብ ሥራ ሌሎች ቅርሶችን ለመጠበቅ ተሞክሮ የሚወሰድበት መሆኑን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ከሐረሪ ክልል ባህል ቱሪዝምና ቅርስ ቢሮ በመተባበር በጁገል ዓለም ዓቀፍ ቅርስ አስተዳደር፣ ጥበቃና ዘላቂ ልማት ዙሪያ ለባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና እየሰጠ ይገኛል።


 

በመድረኩ ላይ የተገኙት የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ህይወት ኃይሉ እንደተናገሩት፤ የክልሉ መንግሥት ኅብረተሰቡን በማስተባበር እያከናወነ ያለው ሥራ አበረታች ከመሆኑ ባለፈ ለሌሎች አካባቢዎችም ልምድ የሚቀሰምበት ነው።

በኢትዮጵያ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ከተመዘገቡት ቅርሶች መካከል የጁገል ዓለም ዓቀፍ ቅርስ አንዱ መሆኑን አውስተዋል።

የሰው ልጆች የጋራ ኃብት የሆነውን ቅርስ ከሚደርስበት አደጋ ለመታደግ የተቀናጀ ጥረት ያስፈልጋል ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ፤ የጁገል ዓለም ዓቀፍ ቅርስን በመጠበቅ ለመጪው ትውልድ እንዲተላለፍ የሚከናወኑ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።

ባለሥልጣኑ የጁገል ዓለም ዓቀፍ ቅርስን የመጠበቅና የመንከባከብ ሥራ እና ነዋሪው ከቅርሱ ተጠቃሚ እንዲሆን እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

የሐረሪ ብሔራዊ ጉባዔ አፈ ጉባዔ አቶ ሙህየዲን አህመድ በበኩላቸው የጁገል ዓለም ዓቀፍ ቅርስን ለነዋሪውና ለጎብኚው ምቹ የማድረግና የማልማት ሥራዎቹ ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል።

የክልሉ መንግሥትና ኅብረተሰቡ በጋራ ባከናወኑት ሥራ ቅርሱ እንዲጠበቅ ከማድረግ ባሻገር የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምር አስተዋጽኦ ማድረጉን ገልጸዋል።

የክልሉ ባህል፣ ቱሪዝምና ቅርስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተወለዳ አብዶሽ ከጁገል ዓለም ዓቀፍ ቅርስ በተጨማሪ በክልሉ የሚገኙ ታሪካዊና ጥንታዊ ቅርሶችን የመንከባከብና የመጠበቅ ሥራዎች በሰፊው መከናወናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም