የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደንበኞች አገልግሎት ወር አስጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የደንበኞች አገልግሎት ወር አስጀመረ

አዲስ አበባ፤ ታኅሣሥ 24/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ "የላቀ አገልግሎት ደስተኛ ደንበኛ" በሚል መሪ ሀሳብ ለአንድ ወር የሚቆይ የደንበኞች አገልግሎት ወር በይፋ አስጀመረ።
በመርኃግብሩ ማስጀመሪያ የገንዘብ ሚኒስትርና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አህመድ ሽዴ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቤ ሳኖ እና የባንኩ ከፍተኛ አመራሮችና ሰራተኞች ተገኝተዋል።
ከታህሳስ 24 እስከ ጥር 25 ለአንድ ወር በሚቆየው በዚህ መርኃግብር በባንኩ አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ከደንበኞች ጋር ውይይት፣ ለአንድ ሳምንት የሚቆይ አወደ ርዕይ እና ለደንበኞች ምስጋና የሚቀርብበት መሆኑ ተመላክቷል።