ኢትዮጵያ እና የዓለም ባንክ የ700 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የፋይናንስ ስምምነት ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ እና የዓለም ባንክ የ700 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የፋይናንስ ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 24/2017(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ እና የዓለም ባንክ የፋይናንስ ዘርፉን ለማጠናከር የ700 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የብድር ስምምነት ተፈራርሙ።
ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ እና የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ፣ የሱዳንና የደቡብ ሱዳን ዳይሬክተር መሪየም ሳሊም ፈርመውታል።
የብድር ስምምነቱ ለፋይናንስ ዘርፍ ማጠናከሪያ ፕሮጀክት የሚውል ነው።
ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያን የፋይናንስ ዘርፍ ዘላቂነትና መረጋጋት ማሻሻልን አላማ ያደረገ ነው።
ፕሮጀክቱ ቁልፍ የሚባሉ የፋይናንስ ዘርፍ ሪፎርሞች እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የካፒታልና የፋይናንስ መዋቅር ለማረጋጋት ለሚደረጉ ጥረቶችን ለመደገፍ ስትራቴጂካዊ በሆነ ሁኔታ መዘጋጀቱ ተገልጿል።
ገንዘቡ መንግሥት በቅርቡ የባንኩን ዘርፍ ለማዘመንና የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ የፈቀደበት ጠንካራ ሪፎርም እንደሚደግፍ የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
መንግሥት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዕዳ ለመክፈልና የባንኩን ካፒታል ለማሳደግ የ900 ቢሊዮን ብር ቦንድ ማውጣቱ ይታወቃል።
አብዛኛው የስምምነቱ ፋይናንስ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የካፒታል መዋቅር የማስተካከያ ሥራዎች ላይ እንደሚውል ተመላክቷል።
በዚህም ለዕዳ ጉዳዮች መፍትሄ የመስጠት፣ የባንኮቹን ብድር የማስመለስ አቅምን ማሳደግ እና የፋይናንስ ተቋማት የካፒታል መጠን (ብድርን ጨምሮ) የተመለከቱ የቁጥጥር መመሪያዎች ተገዢነትን የማረጋጋጥ ሥራ እንደሚከናወን ሚኒስቴሩ ገልጿል።
በተጨማሪም ብድሩ የባንክ ዘርፉን የክትትል እና የህግ ማዕቀፍ በማጠናከር የፋይናንስ መረጋጋትን ይበልጥ የማጎልበት ሥራዎች ላይ ይውላል።
መንግሥት የስራ እድል ፈጠራ እና ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገትን ለማሳለጥ የሚያስፈልግ ካፒታልን ተደራሽ ለማድረግ እያደረጋቸው ያሉ ጥረቶችንም እንደሚያግዝ ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።