በአምስት ወራት ውስጥ ከ167 ሺህ በላይ አዳዲስ ደንበኞች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ሆኑ - ኢዜአ አማርኛ
በአምስት ወራት ውስጥ ከ167 ሺህ በላይ አዳዲስ ደንበኞች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ሆኑ
አዲስ አበባ፤ ታኅሣሥ 24/2017(ኢዜአ)፦ ባለፉት አምስት ወራት ከ167 ሺህ 900 በላይ አዳዲስ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረጉን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገለጸ።
የደንበኞችን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ፍላጎት ጥራት በማረጋገጥ ተደራሽነትን ለማስፋት እየተሰራ እንደሚገኝ አገልግሎቱ ገልጿል።
የአገልግሎቱ የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ መላኩ ታዬ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አገልግሎቱ የኃይል አስተማማኝነትና ፍትሕዊ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ ነው።
በተያዘው በጀት ዓመት 600 ሺህ አዳዲስ ደንበኞችን ተጠቃሚ ለማድረግ ታቅዶ ባለፉት አምስት ወራት 167 ሺህ 952 ደንበኞች ተጠቃሚ አድርጓል ብለዋል።
ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ35 ሺህ 890 ደንበኞች ብልጫ እንዳለው ገልጸው፤ 42 አዳዲስ የገጠር ቀበሌና ከተሞችን ተጠቃሚ ስለመሆናቸው ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ከአሌክትሪክ መስመር ርቀት የሚገኙ ዜጎችን በፀሐይ ኃይል አማራጭ ተጠቃሚ ለማድረግ በአምስት ወራት ውስጥ 25 ስፍራዎች ላይ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ግንባታ ተገንብቶ 74 ሺህ 222 ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም ጠቁመዋል።
በዚህም የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት ተጠቃሚ ደንበኞችን ቁጥር ከ4 ሚሊየን 941 ሺህ በላይ መድረሱን አስረድተዋል።
"የኤሌክትሪክ ቆጣሪ ሥርጭት በአንድ ቀን" በሚል ንቅናቄ የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን አገልግሎትን ለማሳለጥ እየተሰራ ነውም ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በሀገር አቀፍ ደረጃ በአጠቃላይ 8 ሺህ 245 ከተሞችና የገጠር ቀበሌዎች የአሌክትሪክ ተጠቃሚ መሆናቸውን የአገልግሎቱ መረጃ ያመለክታል።