ቀጥታ፡

በስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ዘርፎች የሚከናወኑ ሥራዎች ለኢኮኖሚ ዕድገቱ የድርሻቸውን እየተወጡ ነው - በለጠ ሞላ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 23/2017(ኢዜአ)፡- በስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ዘርፎች የሚከናወኑ ሥራዎች ለሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና የተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስትዩቲትና የእንጦጦ ኦብዘርቫቶሪ ማዕከል የሥራ እንቅስቃሴን ተመልክተዋል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) የሰብል ክትትል፣ የመሰረተ ልማት አገልግሎት፣ የአደጋ መከታተያ እና የዲጂታል ካርታ አገልግሎት ማዕከላት ጨምሮ በስፔስ ሳይንስ እና ጂኦስፓሻል ዘርፎች የሚሰሩ ሥራዎች አበረታች ነው ብለዋል።

እነዚህ ሥራዎች አጠናክሮ በማስቀጠል ሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገቱን ይበልጥ እንዲደግፉ ማድረግ ይገባል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ወደፊት በምድር ብቻ ሳይሆን በህዋ ላይ ያላትን ኃብት ለመጠቀምና ለዕድገት ለማዋል ዛሬ ላይ የቴክኖሎጂ አቅምን አሟጦ መጠቀም እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ኢኒስቲትዩቱ ኢትዮጵያ ከዘርፉ የምትጠብቀውን ውጤት ለማሳካት ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በትብብር መስራት እንዳለበትም አመልክተዋል።

ተቋሙ ኢትዮጵያ በዘርፉ የተማረ ትውልድ ለመፍጠር ከታችኛው የትምህርት እርከን እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በትብብር መስራት እንደሚገባው አሳስበዋል።

የስፔስ ሳይንስና ጂኦስፓሻል ኢንስትዩቲት ዋና ዳይሬክተር አብዲሳ ይልማ በዘርፉ ከምድር እስከ ህዋ ጽንሰ ሀሳብን መሰረት በማድረግ ቴክኖሎጂን በስፋት ጥቅም ላይ የማዋል እንዲሁም የተቋማዊና የሰው ኃይል አቅም ግንባታ ላይ በትኩረት በመስራት ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን አመልክተዋል።

ዘርፉ ትልቅ በጀት የሚጠይቅ በመሆኑ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ዋና ዳይሬክተሩ መግለፃቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።

#Ethiopia

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም