የክልሉ ወጣቶች የኢትዮ ኮደርስ ስልጠናን በመውሰድ ከወቅቱ ቴክኖሎጂ ጋር ሊጓዙ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የክልሉ ወጣቶች የኢትዮ ኮደርስ ስልጠናን በመውሰድ ከወቅቱ ቴክኖሎጂ ጋር ሊጓዙ ይገባል
ሠመራ ታህሳስ 23/2017 (ኢዜአ)፡- የአፋር ክልል ወጣቶች የኢትዮ ኮደርስ ስልጠናን ባሉበት ቦታና በተመቸ ጊዜ በመውሰድ ከወቅቱ ቴክኖሎጂ ጋር ሊጓዙ እንደሚገባ ተገለፀ።
የፌደራል ኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ድጋፍና ክትትል ቡድን የክልሉን የአምስት ወራት የኮደርስ ስልጠና የስራ አፈፃፀምን በተመለከተ ከክልሉ ስትሪንግ ኮሚቴና ስልጠናውን ከወሰዱ የመንግስት ሰራተኞች ጋር ተወያይቷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የድጋፍና ክትትል ቡድን መሪና በኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የብሔራዊ ኤሌክትሮኒክስ፣ መንግስት ልማትና አስተዳደር ዴስክ ኃላፊ አቶ ቴዎድሮስ ታዘዘ፤ የክልሉ ኢትዮ ኮደርስ ስልጠና ወጣቶች ላይ ይበልጥ ትኩረት በማድረግ ተግባሩን እንዲወጣ አሳስበዋል።
የክልሉ ወጣቶች የኢትዮ ኮደርስ ስልጠናን ባሉበት ቦታና በተመቸ ጊዜ በመውሰድ ከወቅቱ ቴክኖሎጂ ጋር ሊጓዙ እንደሚገባም መክረዋል።
''የስልጠና ተደራሽነትን አውን ለማድረግም በትምህርት ቤቶች ላይ ትኩረት መደረግ አለበት'' ያሉት ደግሞ በትምህርት ሚኒስቴር የአይ ሲ ቲና ዲጂታል ትምህርት ክፍል ስፔሻሊስትና የድጋፍና ክትትል ቡድኑ አባል አቶ ከድር ኡርጂ ናቸው።
በዚሁ መድረክ ላይ የተገኙት የክልሉ ኢትዮ ኮደርስ አፈፃፀም ስትሪንግ ኮሚቴ አባልና የክልሉ መንግሥት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ መሐመድ ዓሊ በበኩላቸው ስልጠናው ቴክኖሎጂን በመጠቀም መወዳደር፣ መተግበርና መጠቀም የሚችሉ ወጣቶችን ለማፍራት ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።
''በመሆኑም በስልጠናው ለሚመጣው ስኬት እውን መሆን ጠንክረን እንሰራለን'' ብለዋል።
ስልጠናው ስራቸውን በውጤታማነት ለማከናወን እንዳገዛቸው የገለጹት ደግሞ የመንግስት ስራተኛው ከድር ኢድሪስ ናቸው።
በክልሉ የኢትዮ ኮደርስ ስልጠና በአምስት ወራት ጊዜ ውስጥ ለ1 ሺህ 300 ሰዎች መሰጠቱንም በመረጃው ተመላክቷል።