ቀጥታ፡

የሃይማኖት ተቋማት ለሰላማዊና የተረጋጋ ማህበረሰብ ግንባታ አዎንታዊ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል- አቶ መሀመድ እድሪስ

አዲስ አበባ፤ ታኅሣሥ 23/2017(ኢዜአ)፦ በሁሉም መስክ ሰላማዊና የተረጋጋ ማህበረሰብ እንዲኖር የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚናቸውን እንዲወጡ የሰላም ሚኒስትሩ አቶ መሀመድ እድሪስ ጠየቁ።

የሰላም ሚኒስትር አቶ መሀመድ እድሪስ ከኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል አመራሮች ጋር ትውውቅና ውይይት አድርገዋል።

ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የሃይማኖት ተቋማት ትብብርና አብሮነት ለሰላም ግንባታ ሂደት ትልቅ ሚና አለው።

በመሆኑም በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ ጉዳይ ሰላማዊና የተረጋጋ ማህበረሰብ እንዲኖር የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ አስተዋፆ ሊኖራቸው ይገባል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል በሰላም ግንባታ ስራዎች ላይ እያከናወነ ያለውን ተግባር አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አመልክተዋል።

የሰላም ሚኒስቴር ከካውንስሉ ጋር በትብብርና በቅንጅት ለመስራት ያለውን ዝግጁነትም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ፕሬዚዳንት ጣሰው ገብሬ (ዶ/ር) በበኩላቸው ከመገፋፋት ይልቅ በመተባበር እና በመደጋገፍ ለሀገራችን ሰላም መረጋገጥ ሃይማኖቶች ትልቅ አቅም ሊሆኑ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ካውንስሉ ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በሰላም ግንባታ ስራዎች ላይ የነበረውን ትብብር በማጠናከር ለሀገር ሰላም መረጋገጥ የበኩሉን ሚና እንደሚወጣ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም