አገልግሎቱ በመድሃኒት አቅርቦት ሰንሰለት ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ተከታትሎ ማረም አለበት- ቋሚ ኮሚቴው - ኢዜአ አማርኛ
አገልግሎቱ በመድሃኒት አቅርቦት ሰንሰለት ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ተከታትሎ ማረም አለበት- ቋሚ ኮሚቴው
አዲስ አበባ፤ ታኅሣሥ 23/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት በመድሃኒት አቅርቦት ሰንሰለት ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶች እንዲታረሙ ተገቢውን ቁጥጥርና ክትትል እንዲያደርግ የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮጵያ መድኒት አቅራቢ አገልግሎት የክዋኔ ኦዲት ግኝት ሪፖርት ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።
ሪፖርቱ የ2015/2016 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ መድኒት አቅርቦት ሰንሰለት አስተዳደር አፈፃፀም የክዋኔ ኦዲት ላይ ያተኮረ ነው።
የመንግስት ወጪ አስተዳርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሺመቤት ደምሴ (ዶ/ር)፤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ተቋሙ በአቅርቦት ሰንሰለት ውስጥ አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር ቁጥጥርና ክትትል ማድረግ ይጠበቅበታል።
በኦዲት ግኝቱ በብልጫና በጉድለት የተመዘገበበት ሃብት በመኖሩ የሚመለከተውን አካል ተጠያቂ በማድረግ የእርምት እርምጃ መውሰድ እንደሚገባውም ነው የጠቆሙት።
ተቋሙ የመድሃኒት አቅርቦትና ፍላጎትን ለማጣጣም ባቀደው ልክ ያለመፈጸም ችግሮች የታዩበት በመሆኑ ክፍተቶቹን ለይቶ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ከመድሃኒት መጋዘኖች ተስማሚነት አንፃር የሚታየውን አለመጣጣም ለማስተካከልም በትኩረት መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል።
የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሰረት ዳምጤ በበኩላቸው፤ ተቋሙ የኦዲት ግኝቶችን ተቀብሎ ለማስተካከል የሄደበት ርቀት አበረታተዋል።
ተቋሙ ከመድሃኒትና መሳሪያ ግዥ ጋር ተያይዞ ፍላጎቱን ለግዥ ኤጀንሲ አለማቅረቡ በኦዲት ግኝቱ የተቀመጠ ክፍተት በመሆኑ በቀጣይ እንዲያስተካክል አሳስበዋል።
ዘመናዊ፣ ውጤታማና በጥናት ላይ የተመሰረተ ዘላቂ የመድሃኒት አቅርቦት ስራን መፈጸም እንዳለበትም ጠቅሰዋል።
መድሃኒቶት ጥራታቸውን የጠበቁ እና በተያዘላቸው ጊዜና ሰዓት ተደራሽ ለማድረግም ከባለድርሻ አካላት ጋር ተናቦ መስራት አለበት ብለዋል።
የመድሃኒት ማጓጓዣና ማስቀመጫዎች ላይም ጥንቃቄ የተሞላበት ተግባራትን ማከናወን እንደሚገባ አመላክተዋል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬሕይወት አበበ በበኩላቸው፤ ተቋሙ ለ23 ሺህ የመንግስት ጤና ተቋማት እና 15 በመቶ ለሚሆኑ የግል ሆስፒታሎች መድሃኒት ያቀርባል ብለዋል።
አገልግሎቱ ጥራቱን የጠበቀ መድሃኒት ግዥ የመፈጸም እና የማከማቸት ሂደቱን ማሳለጥ እንዳለበት ጠቅሰው፥ የኦዲት ግኝቶቹ እንዲስተካከሉ ጤና ሚኒስቴር አጋዥ ሚና ይወጣል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ በበኩላቸው፤ የመድሐኒትና የሕክምና መሳሪያ ግዥ ትንበያን አስመልክቶ ተቋማት የሚያቀርቡት ጥያቄ ካላቸው በጀት ጋር አለመጣጣሙ ክፍተት እንዲፈጠር ማድረጉን ገልፀዋል።
ይህን ክፍተት ለማስተካከል በአዲሱ አዋጅ መሰረት ውል የተገባለት የአቅርቦት ስርዓትን በመከተል እንደሚፈጸም አመላክተዋል።