ተቋማቱ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
ተቋማቱ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ
አዳማ፤ ታህሳስ 23/2017 (ኢዜአ) ፡-የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ ።
የመግባቢያ ስምምነቱን የተፈራረሙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) እና የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ተስፋዬ ናቸው።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) እንደገለፁት፤ መገናኛ ብዙሃን በዘርፉ የተለያዩ ማህበራዊ አጀንዳዎች ላይ የተገኙ ውጤቶችና ተሞክሮዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል የጎላ ድርሻ አላቸው።
በተለይ በሚስተዋሉ ክፍተቶች ላይ የመፍትሔ ሃሳቦችን፣ ዘገባዎችና ፕሮግራሞችን በመስራትና በመጠቆም ረገድ እያከናወኑ ያለው ተግባር የሚያስመሰግን ነው ብለዋል።
በቀጣይ ከመገናኛ ብዙሃንና ከሚዲያ ተቋማት ጋር ያለውን ቅንጅት ለማጠናከር የመግባቢያ ስምምነቱ ሚና የጎላ መሆኑን አመልክተዋል።
ወደፊት በተቋማቱ መካከል የሚቋቋመው ፎረምም መገናኛ ብዙሃኑ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትን አጉልቶ ለማሳየት፣ በወቅታዊና ትክክለኛ መረጃ የዳበረ ማህበረሰብን ለመፍጠር በሙያቸው እንዲተባበሩ ለማድረግ እንደሚረዳም ገልፀዋል።
በቀጣይም ፎረሙን መሰረት ያደረጉና ዘርፉን የሚመለከቱ የይዘት ስራዎች ስትራቴጂና የድርጊት መርሃ ግብር ይቀረፃሉ ያሉት ሚኒስትሯ የጋራ የክትትልና የቁጥጥር ተግባራትን የሚያጠናክሩ አሰራሮች ይዘረጋሉ ብለዋል።
ተቋሙን በአግባቡ አግዘው ውጤት ለሚያመጡ የሚዲያ ተቋማት ዕውቅና የሚሰጥበት አሰራር እንደሚኖርም ሚኒስትሯ አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ተስፋዬ በበኩላቸው ባለስልጣኑ የሚዲያ ባለሙያዎችን ክህሎትና አቅም ለማሳደግ ስልጠና ከመስጠት ጀምሮ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
ለዚህም የተለያዩ የስልጠና ማኑዋሎች ተዘጋጅተው ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው ባለስልጣኑ ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት ለመስራት የተፈራረመው የመግባቢያ ስምምነት ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።
የጋራ ፎረሙ ተመስርቶ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሲጀምር በተቋማቱ መካከል ያለውን በትብብር የመስራት ሂደት እንደሚያጠናክረውም ገልፀዋል።