በክልሉ የጨቅላ ሕፃናት ሞትን ለመቀነስ እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል -ቢሮው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የጨቅላ ሕፃናት ሞትን ለመቀነስ እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል -ቢሮው
ደሴ፤ ታህሳስ 23/2017 (ኢዜአ)- በአማራ ክልል የጨቅላ ሕፃናት ሞትን ለመቀነስ እየተደረገ ያለው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ጤና ቢሮ ገለጸ።
በሳምባ ምች እና ያለ ዕድሜያቸው በመወለዳቸው ምክንያት የሚሞቱ ጨቅላ ሕፃናት ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በኮምቦልቻ ከተማ ተካሄዷል።
የጤና ቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አበበ ተምትሜ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ በክልሉ የጤና ተቋማትን በማስፋፋትና ግብዓት በማሟላት የጨቅላ ህፃናት መጠነ ሞትን መቀነስ ይገባል።
በክልሉ ከሚወለዱ አስር ሕፃናት መካከል አንዱ ያለቀኑ ቀድሞ የሚወለድ ሲሆን፤ ከውልደት በኋላም ለሞት የሚጋለጡ ህፃናት መኖራቸውን ተናግረዋል።
በየደረጃው ያሉ ጤና ተቋማትን በመደገፍ፣ የጤና ባለሙያዎችን በማሰልጠንና የኅብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ በዚህ ምክንያት የሚሰተውን የጨቅላ ህፃናት ሞት መቀነስ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በዚህ ረገድ እየተሰሩ ያሉ አበረታች ሥራዎች በማስፋት የጨቅላ ሕፃናት ሞትን ለመቀነስ እየተደረገ ያለው ጥረት ሊጠናከር እንደሚገባው አቶ አበበ ገልጸዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ጌታቸው በለጠ በበኩላቸው ያለ ዕድሜ በመወለድና በሳምባ ምች በሽታ የሚሞቱ ጨቅላ ሕፃናትን ለመቀነስ የተሰራው ሥራ መሻሻል እየታየበት ነው ብለዋል።
እናቶችና ሕፃናት ብቻ የሚገለገሉበት የጤና ማዕከል ከማዘጋጀት ባለፈ አስፈላጊ የሕክምና ግብዓትና የሰው ኃይል በማሟላት ለኅብረተሰቡ አገልግሎት መሰጠቱ ለተገኘው መሻሻል በምክንያትነት ጠቅሰዋል።
የደሴ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ሃይማኖት አየለ እንዳሉት፤ በሆስፒታሉ ለእናቶች እና ለሕጻናት ልዩ የጤና አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል።
ይህም ያለ ዕድሜ በመወለድና በሳምባ ምች በሽታ ሊከሰት የሚችል የጨቅላ ሕፃናት ሞት ቀድሞ ለመከላከል እገዛ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
ያለ ዕድሜያቸው የተወለዱ ሁለት ልጆቻቸው የጤና ችግር ቢገጥማቸውም በተሰጣቸው ልዩ የሕክምና አገልግሎት በአሁኑ ወቅት ጤናቸው በጥሩ ሁኔታ ላይ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አይሻ ዓሊ ናቸው።