የሰላምን አማራጭ የተቀበሉ ታጣቂዎች መመለስ በኢትዮጵያ የትጥቅ እንቅስቃሴ የችግሮች መፍቻ አለመሆኑን የሚያረጋግጥ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሰላምን አማራጭ የተቀበሉ ታጣቂዎች መመለስ በኢትዮጵያ የትጥቅ እንቅስቃሴ የችግሮች መፍቻ አለመሆኑን የሚያረጋግጥ ነው
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 23/2017(ኢዜአ)፡- የመንግስትን የሰላም ጥሪና የህዝብን ድምጽ በመስማት የሰላምን አማራጭ ተቀብለው የመጡ ታጣቂዎች በኢትዮጵያ የትጥቅ እንቅስቃሴ የችግሮች መፍቻ አማራጭ አለመሆኑን የሚያረጋግጥ መሆኑን የሰላም ሚኒስትር ዴዔታ ከይረዲን ተዘራ(ዶ/ር) ገለጹ።
በኢትዮጵያ ለዘላቂ ሰላም ግንባታና ብሔራዊ መግባባት ላይ መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑን በማረጋገጥ ለስኬታማነቱ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ የሰላም ሚኒስትሩ መሐመድ እድሪስ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።
በኦሮሚያና አማራ ክልሎች የተደረጉ ህዝባዊ የሰላም ሰልፎችም አዎንታዊ የሰላም ግንባታ ባህልን በማጎልበት ችግሮችን በምክክር በመፍታት የባህል ሽግግር ለማድረግ ዕድል የሚፈጥሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የህዝብና የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመቀበል በሁለቱ ክልሎች በርካታ ታጣቂዎች የሰላም ጀግኖች በመሆን የሰላም አማራጭን በመቀበል ትጥቃቸውን እያስረከቡ ይገኛሉ።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሰላም ሚኒስትር ዴዔታ ከይረዲን ተዘራ(ዶ/ር)፤ በኢትዮጵያ በተለያዩ አጋጣሚዎች በተፈጠሩ የፖለቲካና የታሪክ ስብራቶች የግጭት አዙሪት ውስጥ በመግባት እስካሁን መዝለቁን ጠቀሰዋል።
የዘመናት የዴሞክራሲ፣ የፍትሕ፣ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችና ብዝኅነትን ለማስተናገድ የነበሩ ውስንነቶች ኢትዮጵያን በግጭት አዙሪት እንድትቆይ ያደረጉ ምክንያቶች መሆናቸውንም አስታውሰዋል።
በመሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመነጋገርና በምክክር መፍትሔ የመስጠት ባህል ባለመዳበሩ ኢትዮጵያ በግጭት አዙሪት ውስጥ በመቆየት የድህነትና የችግር ሰለባ ሆና ቆይታለች ብለዋል።
በመሆኑም መንግስት ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በኢትዮጵያ የነበሩ ስብራቶችን በመጠገን ገዥና አሰባሳቢ ትርክት በመገንባት ሀገራዊ አንድነትንና ዘላቂ ሰላም ለመገንባት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ከምንም በላይ መንግስት ለሰላም ቁርጠኛ በመሆን የጦርነትና ግጭት ምዕራፎች ተዘግተው በሰላማዊ ውይይት ችግሮች በዘላቂነት እንዲፈቱ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።
የሰላም ሚኒስቴርን በማቋቋም ከኢትዮጵያዊነት አውድ በሚመነጭ የጠራ ዕይታ የዜጎች የዳበረና የተሰናሰለ ማኅበረ-ባህላዊ እሴት ለአዎንታዊ ሰላም ግንባታ ጥቅም ላይ እንዲውል እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው ለሰላምና ጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አብራርተዋል።
ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በመሰረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች መግባባትን መፍጠር የሚያስችል ምኅዳር ለማመቻቸት እያከናወናቸው የሚገኙ ተግባራትም ለአዎንታዊ ሰላም ግንባታ መሰረት እንደሚሆኑ አንስተዋል።
በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች የተደረጉ ህዝባዊ የሰላም ሰልፎችም አዎንታዊ የሰላም ግንባታ ባህልን በማጎልበት ችግሮችን በምክክር በመፍታት የባህል ሽግግር ለማድረግ ዕድል የሚፈጥሩ ናቸው ብለዋል።
በጫካ የነበሩ ታጣቂዎችም የህዝብን ድምጽ በመስማት የሚሰጡት አዎንታዊ ምላሽ የትጥቅ ትግል የኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር መፍቻ አማራጭ አለመሆኑን የሚያረጋግጥ መሆኑን ገልጸዋል።
የተለያየ ጥያቄ አለን በሚል ነፍጥ በማንገብ ጫካ የነበሩ ዜጎች የሰላም አማራጭን መከተላቸው የሰላም ጀግኖች በመሆናቸው ለሌሎችም ጥሩ አርአያ መሆናቸውን የሚያመላክት ስለመሆኑም አንስተዋል።
በመሆኑም መንግስት ለዘላቂ ሰላም ግንባታ የሚያከናውናቸውን ተግባራት ማህበረሰቡ፣ የኃይማኖትና ትምህርት ተቋማትን ጨምሮ ሌሎችም እገዛና ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
የተረጋጋ ሀገረ መንግስት በመገንባት በዜጎች መካከል አሰባሳቢ ትርክትን ማጎልበት የሚያስችል የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ የትኩረት መስክ ተቀርጾ እየተሰራ እንደሚገኝም ሚኒስትር ዴኤታው አረጋግጠዋል።