ቀጥታ፡

የኢትዮ-ቱርክዬ ታሪካዊ ወዳጅነት በሁለንተናዊ የዲፕሎማሲ ትብብር መስኮች ተጠናክሮ ይቀጥላል - አምባሳደር በርክ ባራን

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 23/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮ-ቱርክዬ ታሪካዊ ወዳጅነት በሁለንተናዊ የዲፕሎማሲ ትብብር መስኮች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በኢትዮጵያ የቱርክዬ አምባሳደር በርክ ባራን ገለጹ።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢትዮ-ቱርክዬ ወዳጅነት ቡድን በሁለቱ ሀገራት የልማትና የሰላም የዲፕሎማሲ ትብብር መስኮች ተወያይቷል።


 

ውይይቱን አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት በኢትዮጵያ የቱርክዬ አምባሳደር በርክ ባራን፤ በቱርክዬ እና ኢትዮጵያ መካከል ያለው ታሪካዊ ወዳጅነት በሁለንተናዊ የዲፕሎማሲ መስኮች የተቆራኘ ነው ብለዋል።

በተለይም በንግድና ኢንቨስትመንት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግርና ጤና፣ በባህልና በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት መስኮችም የሀገራቱ ትብብር መሰረት እንደሆኑ አስረድተዋል።

በቀጣይም የሀገራቱን ዘመን ተሻጋራ ዘርፈ ብዙ የዲፕሎማሲ ትብብር በማጠናከር የጋራ ተጠቃሚነትን ለማጎልበት በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በቱርክዬ አቀራራቢነት በኢትዮጵያና በሶማሊያ መካከል የተደረሰው ስምምነትም ለምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሰላምና መረጋጋት ወሳኝነት ያለው መሰረታዊ ጉዳይ መሆኑንም አንስተዋል።

የአንካራው ስምምነት የሁለቱንም ሀገራት ትብብር ወደ አዲስ ምዕራፍ በማሸጋገር የሚያጋጥሙ ችግሮችን በሰላማዊ ውይይት መፍትሔ መስጠት እንደሚቻል ማሳያ መሆኑን በአድናቆት ገልጸውታል።


 

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሠላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈትሂ ማህዲ (ዶ/ር)፤ የኢትዮ-ቱርክዬ ታሪካዊ የዲፕሎማሲ ወዳጅነት በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የተመሰረተ ነው ብለዋል።

በምክር ቤቱ የኢትዮ-ቱርክዬ የወዳጅነት ቡድን ያደረገው ውይይትም የሁለቱን ሀገራት ወዳጅነት በሚያጠናክሩና ቀጣናዊ የሰላምና ደኅንነት ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በአንካራ በተደረሰው የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ስምምነት ሂደት ላይ አዎንታዊ ሚና ለተወጡት የቱርክዬ ፕሬዝደንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ላደረጉት አስተዋጽኦ አመስግነዋል።

በፓርላማ ዲፕሎማሲም የኢትዮ-ቱርክዬ ታሪካዊ ወዳጅነት በህዝብ ለህዝብ፣ በባህል፣ በንግድና ኢንቨስትመንት የዲፕሎማሲ ትብብር መስኮች ምክክር መደረጉን አንስተዋል።

በቀጣይም በአንካራ የተደረሰውን ስምምነት ተግባራዊነት የቱርክዬ ድጋፍ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የውይይቱ ተሳታፊዎች ማረጋገጣቸውን አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም