ቀጥታ፡

እየተተገበሩ ያሉ የልማት መርኃ ግብሮች ለስራ እድል ፈጠራ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው - የስራና ክህሎት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 23/2017(ኢዜአ)፡- በሀገሪቱ እየተተገበሩ ያሉ የተለያዩ ልማት መርሃ ግብሮች ለስራ እድል ፈጠራ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ያሉና ብልፅግናን የሚያረጋግጡ መሆናቸውን የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ገለፀ።

ሚኒስቴሩ የዜጎችን ክህሎት በማሳደግ የስራ እድል ተጠቃሚነት ለማስፋት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ሰለሞን ሶካ ለኢዜአ እንዳሉት የኢትዮጵያ ስራ ገበያ መረጃ ስርዓት መዘርጋት የውጭ ሀገር የስራ ስምሪትን ፈጣንና ቀላል አድርጎታል፡፡

በተጨማሪም ለሀገር ውስጥ የስራ እድል ፈጠራ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ውጤት ማስገኘቱን ጠቅሰዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ እየተተገበሩ ያሉ የልማት መርኃ ግብሮችም ለስራ እድል ፈጠራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን አብራርተዋል።

በተለይ ወጣቶች የአምስት ሚሊየን ኢትዮጵያዊያን ኮደሮች ስልጠናን በመውሰድ አለም አቀፍ ተፈላጊነታቸውን ማሳደግ አለባቸው ብለዋል።

የሌማት ትሩፋት፣ የበጋ መስኖ ልማትና የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለስራ እድል ፈጠራ ዕድል ይዘው መምጣታቸውን ተናግረዋል።

በልምድ የተገኘን ሙያ በአጭር ስልጠና በማዳበር እውቅና የመስጠት ስራ እየተሰራ በመሆኑ ዜጎች በዚህ እድል ተጠቃሚ በመሆን ተፈላጊነታቸውን ማሳደግ እንደሚችሉም ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።

አንድ ዜጋ ቢያንስ አንድ ክህሎት በሚል ዜጎች የሙያ ባለቤት ሆነው በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ያላቸውን የስራ እድል ተጠቃሚነት እንዲያሰፉ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

አንድ ምርት በአንድ መንደር የሚል መርኃ ግብር በመተግበርና ምርቶችን ለገበያ በማቅረብ የጋራ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ማህበረሰብ ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም