ቀጥታ፡

ዩኒቨርሲቲው ኢትዮጵያ በአስፈላጊ ቴክኖሎጂዎች ትልቅ አቅም እንድትፈጥር ጉልህ ሚና እየተወጣ ነው - ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 23/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ኢትዮጵያ በአስፈላጊ ቴክኖሎጂዎች ትልቅ አቅም እንድትፈጥር ጉልህ አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) ገለጹ።

ሚኒስትር በለጠ ሞላ(ዶ/ር) እና የሚኒስቴሩ ተጠሪ ተቋማት አመራሮች የዩኒቨርሲቲውን የስራ እንቅስቃሴ ጎብኝተዋል።

ዩኒቨርሲቲው ኢትዮጵያ በአስፈላጊ ቴክኖሎጂዎች ትልቅ አቅም እንድትፈጥር በትምህርትና በምርምር ስራዎች ላይ እየተወጣ ያለው ሚና አይተኬ ነው ሲሉ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው እያከናወነ ያለው ዘርፈ ብዙ ወታደራዊ የምርምር ስራ የመከላከያን ልህቀት በአጭር ጊዜ ውስጥ እውን ማድረግ የሚያስችል ነው ብለዋል።

የሚመለከታቸው ተቋማት መከላከያ ሰራዊት በወታደራዊ የምርምር ዘርፎችና በቴክኖሎጂ ሽግግር ውጤታማ እንዲሆን ከዩኒቨርሲቲው ጋር በቅንጅት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።


 

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በስፔስ ቴክኖሎጂ፣ በአይሲቲ መሰረተ ልማት፣ በሰው ሃብት ልማት እና ሌሎች ዘርፎች ላይ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በትብብር እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ ኮማንዳንት ብርጋዲየር ጀኔራል ከበደ ረጋሣ ዩኒቨርሲቲው ዘርፈ ብዙ የጥናትና ምርምር ስራዎች እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ሚኒስቴሩ እና ተጠሪ ተቋማቱ በሀገር ደረጃ ትልቅ አቅም ያለውን ከፍተኛ ወታደራዊ የትምህርት ማዕከል በዘመናዊ ቴክኖሎጂ እንዲጠናከር ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረባቸውን ከመከላከያ ሰራዊት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም