ፌደራል ፖሊስ ለአገራችን የስፖርት ዘርፍ ማደግ የሚያደርገውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ ይቀጥላል-ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል - ኢዜአ አማርኛ
ፌደራል ፖሊስ ለአገራችን የስፖርት ዘርፍ ማደግ የሚያደርገውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ ይቀጥላል-ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 22/2017(ኢዜአ)፦የፌደራል ፖሊስ ለአገራችን የስፖርት ዘርፍ ማደግ የሚያደርገውን አስተዋጽኦ አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ 116ኛ አመት የምስረታ በዓሉን ምክንያት በማድረግ የውስጥ የስራ ክፍሎች ስፖርታዊ ውድድር ማካሄድ ጀምሯል፡፡
ስፖርታዊ ውድድሮቹ ከዛሬ ጀምሮ እስከ ጥር 4 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያሉ።
እግር ኳስ ፣መረብ ኳስ፣አትሌቲክስ፣ ጠረጴዛ ቴኒስና የገመድ ጉተታ ውድድር የሚካሄድባቸው የስፖርት አይነቶች ናቸው።
በመርኃ ግብሩ ላይ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል፣ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ መኪዩ መሐመድን ጨምሮ የተቋሙ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል በዚሁ ወቅት፤ የፌደራል ፖሊስ ስፖርት ክለብ የኢትዮጵያን ስፖርት በመገንባት ረገድ ስሙ በጉልህ የሚነሳ መሆኑን አስታውሰዋል።
የኢትዮጵያን ስም በአለም አቀፍ መድረክ ከፍ ካደረጉ አንጋፋ ስፖርተኞች መካከል ከፌደራል ፖሊስ ስፖርት ክለብ የተገኙ በርካታ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ክለቡ የነበረውን ታሪካዊ ዝና አስጠብቆ ለመዝለቅ ችግሮች ያጋጥሙት እንደነበር አመላክተዋል።
ፌደራል ፖሊስ በስፖርቱ የነበረውን የቀደመ ዝና በመመለስ ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት ውጤታማ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
ፌደራል ፖሊስ መደበኛ ተግባሩ ከሆነው ወንጀል መከላከል በተጨማሪ ለአገሪቱ የስፖርት ዘርፍ እድገት የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ ነው ያረጋገጡት።
ኮሚሽነር ጀኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል አክለውም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በቅርቡ አመታዊ የፖሊስ ሰራዊት ስፖርት እንደሚያዘጋጅ ተናግረዋል፡፡
ከአመታዊ የፖሊስ ሰራዊት ስፖርት ቀጥሎ በአዲስ አበባ 14 የምስራቅ አፍሪካ አገራት የሚሳተፉበት የፖሊስ ስፖርት ውድድር እንደሚከናወን ገልጸዋል።
ዛሬ የተጀመረው ስፖርታዊ ውድድርም በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ ስፖርተኞችን ለመለየት ሚናው ከፍተኛ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡