የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በቀድሞ የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በቀድሞ የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን ገለጹ
አዲስ አበባ፤ ታኅሳስ 22/2017 (ኢዜአ)፦ የቀድሞ የህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ማንሞሃን ሲንግ የኢትዮጵያ እውነተኛ ወዳጅና ለአገራቱ ትስስር መጠናከር ወሳኝ ሚና የተጫወቱ መሪ እንደነበሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዛሬ አዲስ አበባ በሚገኘው የህንድ ኤምባሲ ተገኝተው በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ህልፈት የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት ሥም በማንሞሃን ሲንግ ህልፈተ ህይወት የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘን ለህንድ ህዝብና መንግሥት ገልጸዋል።
የህንድ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ማንሞሃን ሲንግ ባለ ራዕይ፣ ድንቅ የፖለቲካ መሪ እና ለዓለም ለውጥ ተሟጋች በመሆን ህንድ በዓለም መድረክ ተጽእኖ ፈጣሪ እንድትሆን ባደረጉት ትልቅ አስተዋጽኦ ሲታወሱ ይኖራሉ ብለዋል።
“ሲንግ የኢትዮጵያ እውነተኛ ወዳጅ ነበሩ” ያሉት ሚኒስትሩ የሁለቱን አገራት ትስስር የማጠናከር ሚና መጫወታቸውን አውስተዋል።
ሚኒስትሩ “በዚህ ጥልቅ ሀዘን ውስጥ ከሟች ቤተሰቦች እንዲሁም ከህንድ ህዝብ እና መንግሥት ጋር በአብሮነት እንቆማለን” ሲሉ መግለፃቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።