ቀጥታ፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በጂቡቲ ከኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ተወካዮች ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፤ ታኅሳስ 22/2017 (ኢዜአ)፦ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) በጂቡቲ ከኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ተወካዮች ጋር በተለያዩ ርዕሰ-ጉዳዮች ዙሪያ ምክክር አካሂደዋል።

የኮሚዩኒቲ ተወካዮች በጂቡቲ ሊገነባ ስለታቀደው የኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት ድጋፍ፣ ስለ ዜጎች መብት፣ ስለ ሀገራዊ ጥሪዎች እና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ሀሳብ አንስተዋል።


 

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ኮሚዩኒቲው ለሀገራዊ ጥሪዎች ሲያደርግ ለነበረው ንቁ ተሳትፎ ምስጋና አቅርበዋል።

ወደፊትም እንዲህ ዓይነቱ በጎ አገራዊ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

የኮሚዩኒቲ ትምህርት ቤት ግንባታውን ለመደገፍ ከተዋቀረው ዐብይ ኮሚቴ ጋር በቅርበት እንደሚሰሩም ገልጸዋል።

በጂቡቲ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሚያነሷቸው ጥያቄዎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት እንደሚደረግባቸው ሚኒስትሩ መግለፃቸውን በጂቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም