ቀጥታ፡

በክልሉ የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ለማጎልበት የተጀመሩ ተግባራት ሊጠናከሩ እንደሚገባ ተገለጸ

ዲላ፤ ታህሳስ 22/2017 (ኢዜአ) :- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ለማጎልበት የሚከናወኑ ተግባራት ሊጠናከሩ እንደሚገባ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፀሃይ ወራሳ ገለፁ።

በክልሉ "ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለእምርታዊ እድገት" በሚል መሪ ሀሳብ የሴቶችን ማህበራዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ላይ ያተኮረ የንቅናቄ መድረክ በዲላ ከተማ ተካሂዷል።


 

የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፀሃይ ወራሳ በወቅቱ እንዳሉት በክልሉ የሴቶችን የኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ርብርብ መደረግ አለበት። 

በተለይ ክልሉን የልማትና የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የሴቶች እኩል ተሳታፊነትና ተጠቃሚነትን ማጎልበት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ በከተማ ግብርና፣ በሌማት ትሩፋትና በመሰል የልማት ዘርፎች የተሳተፉ ሴቶች አመርቂ ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑንም አፈ ጉባኤዋ አንስተዋል።

''ይህንኑ ስኬት በሴት ተማሪዎች የትምህርት ውጤት መሻሻልና በእናቶች ጤና ላይ መድገም አለብን'' ያሉት አፈ ጉባኤዋ የተጀመሩ ተግባራት ከግብ እንዲደርሱ በየደረጃው የሚገኙ ሴቶች መትጋት እንዳለባቸው አመላክተዋል።


 

የክልሉ ሴቶች ለልማትና እድገት የነቃ ተሳትፎ ከማድረግ ባለፈ ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የሴቶች ሊግ ሀላፊ ወይዘሮ እቴነሽ በየነ ናቸው።

አሁንም በሁሉም ዘርፎች የሴቶችን እኩል ተጠቃሚነትና ተሳታፊነት ከማረጋገጥ አንጻር አሁንም ብዙ ቀሪ ስራዎች መኖራቸውን ነው ያብራሩት።

የንቅናቄ መድረኩም ሴቶች በትምህርትና በጤና ያላቸውን ተሳትፎ ማሳደግ፣ የማህጸን በር ካንሰር ግንዛቤና ምርመራ እንዲሁም የሴት ልጆችን የትምህርት ውጤት ለማሻሻል የጋራ ጥረት ማድረግን ያለመ መሆኑንም ገልጸዋል።

በተጨማሪም የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የቦንድ ግዥ ላይ ያቸውን ተሳትፎ ለማጠናከር ያለመ ነው ብለዋል።


 

የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ  ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) በበኩላቸው ሴቶች በስነ-ምግባር የታነጸ፣ ሀገሩን የሚወድ ትውልድ በመቅረጽ ቀዳሚ ድርሻ እንዳላቸው አመልክተው የዞኑ አስተዳደርም የሴቶችን እኩል ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

ለአንድ ቀን በተዘጋጀው መድረክ የክልልና የዞን ሴት የስራ ሃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳታፊ ሆነዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም