የኮሪደር ልማቱ የከተማዋን የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ችግርን በከፍተኛ ሁኔታ እየቀረፈ ነው - ኢንጂነር ሽፈራው ተሊላ - ኢዜአ አማርኛ
የኮሪደር ልማቱ የከተማዋን የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ችግርን በከፍተኛ ሁኔታ እየቀረፈ ነው - ኢንጂነር ሽፈራው ተሊላ
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 22/2017(ኢዜአ)፡- በአዲስ አበባ እየተገነቡ ያሉ ኮሪደር ልማት ስራዎች የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ችግርን በከፍተኛ ሁኔታ እየቀረፈ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሽፈራው ተሊላ(ኢ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሽፈራው ተሊላ(ኢ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ የኃይል መቆራረጥ በህብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ቅሬታ እንደሚፈጥር አውስተዋል።
የኃይል መቆራረጥ ከሚፈጥሩ መንስኤዎች መካከል የመሰረተ ልማት ስርቆት፣ የኤሌክትሪክ መስመር በዛፎች መጎዳት፣ የምሰሶ ማርጀት፣ የኤሌክትሪክ ገመድ በአግባቡ አለመዘርጋት ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም በጥናት ላይ የተመሰረተ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ገልጸው፥ በአዲስ አበባ እየተተገበረ ያለው የኮሪደር ልማትም የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማትን እያሻሻለ መምጣቱን አንስተዋል።
በተለይም የኃይል መሰረተ ልማቶች ደረጃውን በጠበቀ መልኩ እንዲዘረጉና አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እንዲፈጥሩ ማስቻሉን አስረድተዋል።
የኮሪደር ልማት በሚሰራባቸው አካባቢዎች የኤሌክትሪክ መስመሮች ለብልሽት ከሚዳርጉ ነገሮች በጸዳ መልኩ መዘርጋታቸውን አንስተው፥ ይህም ቀደም ሲል ሲያጋጥም የነበረውን የመቆራረጥ ችግር እየቀረፈ ነው ብለዋል።
ከተማዋ የአፍሪካ መዲናና የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ እንደመሆኗ 24 ሰዓት ያልተቋረጠ የኃይል አቅርቦት እንዲኖራት የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
የኤሌክትሪክ መቆራረጥ አሁንም አልፎ አልፎ እንደሚያጋጥም ጠቅሰው፥ ይህንን በዘላቂነት ለመፍታትና የከተማዋን ከፍተኛ የኃይል ፍላጎት ለማሟላት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የኃይል ብክነትን ከመከላከል አኳያ በከተማዋ ጎዳናዎችና ህንጻዎች ላይ የሚተከሉ መብራቶች ኃይል ቆጣቢ መሆናቸውንም ዋና ስራ አስፈጻሚው አመልክተዋል።