ቀጥታ፡

የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶችን በጥራትና በፍጥነት በማጠናቀቅ ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ ነው - የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 22/2017(ኢዜአ)፡- የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶችን በጥራትና በፍጥነት በማጠናቀቅ ወደ ስራ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የመስኖና ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ምርታማነት ጉባኤ ከየካቲት 5 እስከ 7 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

አለም አቀፍና አህጉር አቀፍ የዘርፉ ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበትን ጉባኤ በስኬት ለማስተናገድ የብሄራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ ዝግጅት ማስጀመሪያ መርኃ ግብር የውይይት መድረክ ተካሂዷል።


 

በዚህ ወቅት የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ(ዶ/ር) እንዳሉት በሀገሪቱ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ረገድ ክፍተቶች ሲስተዋሉ ቆይተዋል፡፡

ይህንኑ ችግር ለመፍታትና የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶችን በፍጥነት በማጠናቀቅ ውጤት ለማስመዝገብ የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ተቋቁሞ ስራውን እየመራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

በዚህም ካለፈው አመት መጨረሻ አንስቶ የማሻሻያ ስራዎች እንዲሰሩ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የተሻለ የፕሮጀክት አስተዳደር፣ የአመራርና የአሰራር ስርአት ተዘርግቷል ብለዋል።

በማሻሻያዎቹ በፕሮጀክቶች ላይ ይታይ የነበረውን የጥራትና ፍጥነት ችግር በመፍታት ወደ ስራ ለማስገባት የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።

በተያዘው 2017 ዓ.ም ሶስት ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑንም ጨምረው ጠቁመዋል፡፡

የልማት አጋሮችና ባለሃብቶች በመስኖ ልማት ላይ እንዲሰማሩ ከክልሎች ጋር በመተባበር እየተሰራ መሆኑንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

በቆላማ አካባቢዎች የነበሩ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ለመጨረስ እንዲሁም ተጨማሪ የማስፋፊያ እቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ አሀጉራዊና ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን በተሳካ መልኩ በማስተናገድ ተመራጭ መሆኗን አንስተው ጉባኤው ስኬታማ እንዲሆን ከወዲሁ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ጉባኤው የኢትዮጵያ የመስኖ ልማትና የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም እየተሰሩ ያሉ የአረንጓዴ አሻራ፣ የስንዴ ልማትና የሌማት ትሩፋት ስራዎችን ለአለም ለማስተዋወቅና ለገፅታ ግንባታ ያለው ሚና የላቀ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ልምድ መጋራት የሚያስችል እንደሚሆንም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም