በዲጂታል ዘርፍ ኢትዮጵያን የሚያስጠሩ ብቁና ተወዳዳሪ ወጣቶችን ማፍራት ላይ ትኩረት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በዲጂታል ዘርፍ ኢትዮጵያን የሚያስጠሩ ብቁና ተወዳዳሪ ወጣቶችን ማፍራት ላይ ትኩረት ተደርጓል
አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 22/2017(ኢዜአ)፡- በዲጂታል ዘርፍ ኢትዮጵያን የሚያስጠሩ ብቁና ተወዳዳሪ ወጣቶችን ማፍራት ላይ ትኩረት መደረጉን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለምፀሐይ ጳውሎስ ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ያስጀመሩት የ5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደሮች ኢኒሼቲቭ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ትግበራን ለማሳካት ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የ5 ሚሊዮን ኮደሮች ስልጠና ኢኒሼቲቭ የመጀመሪያ ዙር ማጠቃለያ መርኃግብርን አካሂዷል።
በመርኃ ግብሩ ሥልጠናውን ያጠናቀቁ የኢንስቲትዩቱ አመራሮች፣ ሠራተኞች እና በተለያዩ ትምህርት ቤቶች የተቋቋሙ የኤ አይ (AI) ክለብ አባላት ተመርቀዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ዓለምፀሐይ ጳውሎስ በመርኃ ግብሩ ባስተላለፉት መልዕክት፤ መንግሥት የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማፋጠን ለዲጂታል ስርዓት ግንባታ ትኩረት መስጠቱን አንስተዋል።
በዚህም የሰው ኃይልን በማብቃት ረገድ አበረታች ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛል ብለዋል።
በተለይ 5 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ኮደሮች ኢኒሼቲቭ የዲጂታል እውቀትን በማስረፅ ረገድ ጉልህ ሚና አለው ነው ያሉት።
ኢኒሼቲቩ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያስጠሩ ብቁና ተወዳዳሪ ወጣቶችን ለማፍራት በመንግሥት የተጀመረውን ጥረት የሚያሳካ እንደሆነም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና(ዶ/ር)፥ ኢኒሼቲቩ ከተቋሙ ተልዕኮ ጋር የተሳሰረ መሆኑን ተናግረዋል።
የተሰጠው ስልጠናም ሠራተኞች የቴክኖሎጂ አቅማቸውን እንዲያሳድጉና ተጨማሪ እውቀት እንዲያገኙ ማድረጉን ነው ያብራሩት።
ስልጠናውን ካጠናቀቁ የኢንስቲትዩቱ ሠራተኞች መካከል ቤዛዊት ወንድማገኝ እና አማኑኤል ሁምሳ በስልጠናው በዌብ ፕሮግራሚንግ፣ በአንድሮይድ ማበልፀግ፣ በዳታ ሳይንስና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መሠረታዊ እወቀት መጨበጣቸውን ተናግረዋል።
ለሦስት ዓመታት የሚቆየው የ5 ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ኮደሮች ስልጠና ኢኒሼቲቭ "ትውልድ ይማር፣ ትውልድ ይሰልጥን፣ ከዓለም ጋር ይፎካከር" በሚል እሳቤ ተግባራዊ እየተደረገ ነው።