ባለፈርጀ ብዙ ፋይዳዎች ሀገርኛ ዕደ ጥበባት - ኢዜአ አማርኛ
ባለፈርጀ ብዙ ፋይዳዎች ሀገርኛ ዕደ ጥበባት

ዕደ ጥበባት የአንድ ማህበረሰብ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊ እንዲሁም ስነ ልቦናዊ ማንነት ማንጸባረቂያ ዕሴቶች ተደርገው ይወሰዳሉ።
በቀላል ጥሬ ዕቃዎች እና በባህላዊ መንገድ የሚመረቱ በመሆናቸውም የሀገር በቀል ዕውቀትና የሀገርኛ ጥበብ መገለጫም ናቸው።
እነዚህ ገጸ-ብዙ የሆኑ ዕደ ጥበብ ምርቶች በበርካታ ሀገራት የማህበረሰብ ትዕምርቶችና የቱሪዝም ሀብቶችም ሲሆኑ ይስተዋላል።
ሉላዊነት በተስፋፋበት በዚህ ዘመን ስንኳ አያሌ ሀገራት ጎብኚዎች በተዘዋወሩባቸው ክፍላተ ዓለማት ሁሉ የየማህበረሰቡን ዕደ ጥበብ ውጤቶችን ይሸምታሉ።
ይህ ደግሞ ዕደ ጥበባት ለዝቀተኛው ማህበረሰብ ስራ ዕድል በመፍጠርና የኢኮኖሚ ምንጭ በመሆን አይተኬ ሚና እንዲጫወቱ አድርጓቸዋል።
በሌላ በኩል የሀገር ገጽታ በማጎላት የማይናቅ ፋይዳ አላቸው።
ኢዜአ በባህልና ዕደ ጥበብ ውጤቶችን በማስተዋወቅና በማልማት ለኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማዋል በየአካባቢው ምን እየተከናወነ እንዳለ በተለያዩ ክልሎች ተዘዋውሮ ቅኝት አድርጓል።
የኦሮሚያ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ደራራ ከተማ፤ የክልሉ መንግሥት ተተኳሪ የልማት ዘርፎች አንዱ በሆነው በቱሪዝም መስክ የባህልና ዕደ ጥበብ ውጤቶችን ትኩረት ተሰጥቷቸዋል ይላሉ።
ዕደ ጥበባት ለዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ገቢ በማመንጨትና የህዝቡን ባህል በማስተዋወቅ ጉልህ ሚና እንዳላቸው ይገልጻሉ።
በዚህም የዕደ ጥበብ ምርቶችን በብዛት ለማምረት ይቻል ዘንድ በገጠርም ሆነ በከተማ ሴቶችና ወጣቶችንን ጨምሮ ሙያተኞችን በጎጆ ኢንዱስትሪ እንዲደራጁ መደረጉን ያወሳሉ።
ከማምረት ባሻገርም ከሆቴሎች፣ ከአስጎብኚዎችና ሌሎች ተቋማት ጋር የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው ጥረት ተደርጓል ባይ ናቸው።
በሐረሪ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ቅርስ ቢሮ የባህል ዳይሬክተር አቶ እስክንድር አብዱረሀማን፤ በክልሉ የሚዘወተሩ ከትውልድ ወደ ትውልድ የተሻገሩ የዕድ ጥበባት የማህበረሰቡ መልከ ብዙ ማንነቶችን ያዘሉ እሴቶች እንደሆኑ ይናገራሉ።
የክልሉ መንግስት የዕደ ጥበብ ማሰልጠኛ ኮሌጅ በመመስረትና ባለሙያ በመመደብ በስምንት የዕደ ጥበብ ዓይነቶች ስልጠና እየተሰጠ ስለመሆኑ ያነሳሉ።
ዕደ ጥበብ ውጠቶቹ ከማንነት መገለጫነታቸው ባሻገር ለመስህብነት ውለው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸው እንዲጎለብት የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ ስለመሆኑም እንዲሁ።
የዕደ ጥበብ ውጤቶች ወደ ውጭ በመላክ ምርቶቹን ከማስተዋቅና ከማበልጸግ ባለፈ የውጭ ምንዛሬ እንዲያስገኙ እየተሰራ ነው ይላሉ።
የሐረሪ ጌይ ሞኦት(የአለላ ስፌት) እና ጌይ ከሎይታ(የሐረሪ ባህላዊ ቆብ) ዓለም አቀፍ ዕውቅና አግኝቶ መለያ (ብራንድ) እንደተሰጣቸው ለአብነትይገልጻሉ።
የዕደ ጥበባት በስፋት ከሚታወቅባቸው አካባቢዎች አንዱ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኘው አርባ ምንጭና አካባቢ ይጠቀሳል።
በአርባ ምንጭ ከተማ 'ጃኖ የዕደ ጥበብ ኢንተርፕራይዝ' ማናጀር ተሻለ ጌታቸው፤ ማህበሩ በሀገርኛ ሽመና ምርቶችን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ያቀርባል።
የኢንተርፕራይዙ ነጠላ፣ ጋቢ፣ መጋረጃዎች፣ የአልጋ ልብሶች፣ የጠረጴዛ ማልበሻዎች፣ የአንገት ልብሶች እና ሌሎች አልባሳትን በስፋት በማምረት አባላቱን ተጠቃሚ እያደረገ ነው ይላሉ አቶ ተሻለ።
ማህበሩ በባዛርና ዐውደ ርዕየች ላይ በመሳተፍ ምርቶችን በማስተዋወቅ ተደራሽነቱን እያሰፋ ስለመሆኑ ይገልጻሉ።
በተለይም የቱሪስት መዳረሻ በሆነቸው አርባ ምንጭ መገኘታቸው ዕደ ጥበብና ቱሪዝም እንዴት እንደተሳሰሩ መታዘባቸውን ይጠቅሳሉ።
ሀገርኛ የዕደ ጥበብ ሥራዎች ሰፊውን ህብረተሰብ የሚይዙ በመሆኑ ዘርፉ ይበልጥ ትኩረት ተሰጥቶት ቢሰራበት የሀገር ጥበብና ገጽታ በማጉላት፣ የማህበረሰቡን እሴት በማስተዋወቅና የቱሪዝም ተጨማሪ አቅም በመሆን ፈርጀ ብዙ ፋይዳ እንደሚኖረው ኢዜአ ያነጋገራችው የዘርፉ ተዋኒያን ገልጸዋል።