ቀጥታ፡

የብሔራዊ ቤተመንግስት እድሳት የብልጽግና ፓርቲ አቧራን አራግፎ አሻራን የማኖር ስራ ማሳያ ነው - አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ ፤ ታህሳስ 22/2017(ኢዜአ)፡-የብሔራዊ ቤተመንግስት እድሳት የብልጽግና ፓርቲ አቧራን አራግፎ አሻራን የማኖር ስራ ማሳያ መሆኑን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።

አቶ አደም ብልጽግና ፓርቲ ትላንት የስርዓተ መንግስት አስተዳደራችን አንድ አካል ሆነው ካለፉ ልንቀይራቸው ከማንችላቸው ታሪኮች ጋር ፈፅሞ ፀብ የለውም ሲሉ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።

ፓርቲው በመርህ ደረጃ ከትላንት ተምሮ፣ዛሬን አሳምሮ፣ነገን የተሻለ ማድረግን በማመን የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር በመትጋት ላይ ይገኛል ብለዋል።

የብሔራዊ ቤተመንግስት እድሳት አቧራን አራግፎ አሻራን የማኖር ስራም በዚሁ እሳቤ የተቃኘ መሆኑን አመልክተዋል።

ጥበብ እና ኢትዮጵያ፤ ስልጣኔ እና ኢትዮጵያ፤ ኅብረ-ብሔራዊነት እና ኢትዮጵያ፤ ቀደምትነት እና ኢትዮጵያ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታ የሆኑ በልኳ ተሰፍተው ስሟ ሲጠራ አብረው የሚነሱ ተቀፅላዎቿ መሆናቸውን በስፍራው የተሰደረው መኪናውም፣የንግስና ካባውም፣ ዙፋኑም እና የተለያዩ የሀገራችንን አካባቢዎች የሚገልፁ ስጦታዎችና ሌሎች መገለጫዎች ምስክር ናቸው ብለዋል።

ትላንት ታሪክ ነው! ዛሬ ቅርስ ነው! ነገ ውርስ ነውና እይታችንን ልዕልና መር ጉዞ ላይ በማድረግ ለሁላችንም የምትሆን ኢትዮጵያን ለመፍጠር እንትጋ!! ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም