ቀጥታ፡

ሕዝብ የሚያነሳቸው የአሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥና ፍትሃዊ ተደራሽነት ጥያቄዎች በዘላቂነት ሊፈቱ ይገባል- ምክር ቤቱ

አዲስ አበባ፤ ታኅሣሥ 22/2017(ኢዜአ)፦ በሀገሪቷ የተለያዩ አካባቢዎች ሕዝብ የሚያነሳቸው የኃይል መቆራረጥና ፍትሃዊ ተደራሽነት ጥያቄዎች በዘላቂነት እንዲፈቱ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

የኤሌክትሪክ ኃይልና አገልግሎትን የሚመሩ ተቋማት በበኩላቸው የህዝብ ቅሬታዎችን ለመፍታትና የኢኮኖሚ ዕድገቱን ታሳቢ ያደረገ ዘላቂ ኃይል ለማቅረብ ስትራቴጂ ቀርጸው እየሠሩ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ መሰረት ሃይሌ እንዳሉት የምክር ቤት አባላት ከመረጣቸው ህዝብ ጋር ባደረጉት ውይይት የኤሌክትሪክ ኃይል ፍትሃዊ ተደራሽነትና የመሰረተ ልማት ዝርጋታ እጥረቶች ዋነኞቹ የህዝብ ጥያቄዎች ናቸው።

በአብዛኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች የመብራት ችግር መኖሩንና ይህን ለመፍታት ተቋማቱ ምን አይነት እርምጃ እየወሰዱ እንዳለ የተቋማቱ የስራ ሃላፊዎች በምክር ቤት አባላት ተጠይቀዋል።

የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትና ፍላጎትን ለማጣጣም ምን እየተሠራ እንደሚገኝ የወከሉት ህዝብ መጠየቁን የምክር ቤት አባላቱ አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መንግስት ለኤሌክትሪክ መስመር፣ ለኃይል ማመንጫና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ግንባታ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል።

የኃይል መሰረተ ልማትንና ተደራሽነትን ለማስፋት ጥረት እየተደረገ ቢሆንም ከኢትዮጵያ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትና የህዝቡ የልማት ፍላጎት አኳያ የኃይል ፍላጎትና ተደራሽነቱ ሊጣጣም አለመቻሉን አንስተዋል።


 

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጅነር ሽፈራው ተሊላ፥ ከዋና መስመርና ከተለያዩ የኃይል አማራጮች ህብረተሰቡን የኃይል ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ፍትሐዊ ተደራሽነትን ለማረጋገጥም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለክልሎች በሚመድበው የበጀት ቀመር መሰረት ገጠሩን ተጠቃሚ ለማድረግ የኃይል አቅርቦት እየተስፋፋ እንደሚገኝ ተናግረዋል።


 

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጅነር አሸብር ባልቻ፣ ተቋሙ ከፍተኛ በጀት የሚጠይቁ የኃይል ማስተላለፊያ ጣቢያዎችን እየገነባ ነው ብለዋል።

በዚህም የህዝብ ቅሬታዎችን ለመፍታት እና የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማፋጠን ዘላቂ ኃይል ለማቅረብ ስትራቴጂ ተቀርጾ በመተግበር ላይ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሽፈራው ተሊላ፥ እ.ኤ.አ ከ2018 ጀምሮ መንግስት የገጠር ኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማስፋት በጀት መድቦ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል በ1998 ዓ.ም የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ከተሞች 690 ብቻ እንደነበሩ ጠቅሰው፥ አሁን ላይ 8 ሺህ 240 ደርሰዋል ብለዋል።

ይሁንና ካለው ከፍተኛ ፍላጎትና ተደራሽነትን ለማስፋት የግንባታ ግብዓት ዋጋ መናርና ሌሎች ችግሮች ፈታኝ መሆናቸውን አንስተዋል።

የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ውድመትና ዝርፊያም ሌላው ተግዳሮት መሆኑን ገልጸዋል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታ መሰረት ኃይሌ፥ ተቋማቱ ካለው የልማት ፍላጎት አኳያ የበጀት እጥረት እንዳለባቸው ቢታወቅም በአገልግሎት አሰጣጥ የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮች ሊፈተሹ ይገባል ብለዋል።

በሌላ በኩል የተመደበን በጀት በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋልና የህዝብን እርካታ መጨመር ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው አስገንዝበዋል።

በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚስተዋለው የመብራት መቆራረጥና የኃይል ፍትሐዊ ተደራሽነት ችግርን በዘላቂነት መፍታት እንደሚገባ የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ዴኤታዋ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም