አምስት ሚሊዮን ኮደሮች ኢንሼቲቭ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ለማፍራት ያስችላል- አለምፀሐይ ጳውሎስ - ኢዜአ አማርኛ
አምስት ሚሊዮን ኮደሮች ኢንሼቲቭ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ለማፍራት ያስችላል- አለምፀሐይ ጳውሎስ
አዲስ አበባ፤ ታኅሣሥ 22/2017(ኢዜአ)፦ አምስት ሚሊዮን ኮደሮች ኢንሼቲቭ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዲጂታል ዘርፍ ብቁና ተወዳዳሪ የሰው ኃይል ለመፍጠር እንደሚያስችል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር አለምፀሐይ ጳውሎስ ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት 5 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ኮደሮች ኢንሼቲቭ የመጀመሪያ ዙር ማጠቃለያ መርኃ ግብር ያካሄደ ሲሆን በዕለቱም ስልጠናውን ያጠናቀቁ የኢንስቲትዩቱ አመራሮች፣ ሠራተኞችና በተለያዩ ትምህርት ቤቶች የተቋቋሙ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ክበብ አባላት ተመርቀዋል።
በመርኃግብሩ ላይ የተገኙት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር አለምፀሐይ ጳውሎስ እንዳሉት፤ መንግሥት ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025ን ዕውን ለማድረግ በልዩ ትኩረት እየሰራ ነው።
ለዚህ ስኬት በዘርፉ የሰው ኃይልን ለማፍራት ከተተገበሩ መርሀ ግብሮች መካከል የአምስት ሚሊዮን ኮደሮች ኢንሼቲቭን ለአብነት ጠቅሰዋል።
ኢንሼቲቩ ኢትዮጵያን በዘርፉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚያደርግ የሰው ኃይል ማፍራት የሚያስችል ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተርና ወርቁ ጋቻና (ዶ/ር) በ5 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ኮደሮች ኢንሼቲቭ ሁሉም የተቋሙ ሠራተኞች የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ያስጀመሩት የ5 ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ኮደሮች ሥልጠና የዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የተያዘውን ጥረት ለማሳካት እየተሰራ ይገኛል።
ፕሮጀክቱ "ትውልድ ይማር፣ ትውልድ ይሰልጥን፣ ከዓለም ጋር ይፎካከር" በሚል እሳቤ ዜጎች የቴክኖሎጂ እውቀታቸውን በማዳበር በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና ብቁ እንዲሆኑ ተግባራዊ እየተደረገ ነው።
ፕሮጀክቱ በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት 5 ሚሊየን ኢትዮጵያውያንን በዌብ ፕሮግራሚንግ፣ በአንድሮይድ ማበልፀግ፣ በዳታ ሳይንስና አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መሠረታዊ የዲጂታል ክህሎት እንዲጨብጡ የሚያስችል ነው።