ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የስነ ምግባር ጥሰት በፈጸሙ 20 አመራርና ሠራተኞች ላይ እርምጃ ወሰደ

አዲስ አበባ፤ ታኅሣሥ 22/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የስነ ምግባር ጥሰት በፈጸሙ 20 አመራርና ሠራተኞች አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰዱን ገለፀ።

የአገልግሎቱ የሥነ ምግባር እና ፀረ-ሙስና ክፍል ዳይሬክተር አቶ ህብረወርቅ ይመኑ እንዳሉት ከደንበኞቹ የመጡ ቅሬታዎችን መሰረት አድርጎ ባደረገው ማጣራት በ20 የተቋሙ አመራርና ሠራተኞች ላይ ከፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እስከ ደመወዝ ቅጣት የሚደርስ አስተዳደራዊ እርምጃ ተወስዷል፡፡

እርምጃው የተሰወደባቸው ባለፉት አምስት ወራት ከትራንስፎርመር አቅም በላይ የኃይል ጭነት በመፍቅድ እንዲቃጠል በማድረግ፣ አዳዲስ ደንበኞችን በሕገ-ወጥ መንገድ በማስተናገድ፣ ነባር ደንበኞችን ለኃይል መቆራረጥ በመዳረግ እና የአገልግሎት ሂሳብ ቀንሰው ተቋሙ ላይ ጉዳት ያደረሱ መሆናቸውን በማረጋገጥ እንደሆነ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል 60 ተጨማሪ ቅሬታዎችን ተቀብሎ እያጣራ መሆኑን ገልፀው፤ የደንበኞች ቅሬታ አቀራረብ በቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን የሞባይል መተግበሪያ እና የድረ-ገፅ ማበልፀግ ሥራ ተጠናቆ የሙከራ ሥራ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የሥነ ምግባር ጥሰት እንዳይፈፀም የቅድመ-መከላከል ስራ ላይ ትኩረት መደረጉንም ጠቁመው፤ በተለይም የአሠራር ሥርዓቱን የማዘመን፣ የሥነምግባር መመሪያዎችን የማሻሻል እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ከአገልግሎቱ ያገኘው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም