አየር መንገዱ በመጪዎቹ ሳምንታት የገና እና የጥምቀት በዓላትን ምክንያት በማድረግ ወደ ላሊበላ እና ጎንደር ከተሞች ተጨማሪ በረራዎች ሊመድብ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አየር መንገዱ በመጪዎቹ ሳምንታት የገና እና የጥምቀት በዓላትን ምክንያት በማድረግ ወደ ላሊበላ እና ጎንደር ከተሞች ተጨማሪ በረራዎች ሊመድብ ነው
አዲስ አበባ፤ታህሳስ 22/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመጪዎቹ ሳምንታት የሚከበሩትን የገና እና የጥምቀት በዓላት ለማክበር በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ ውቅር አብያተ ክርስትያናት ወደሚገኙበት ላሊበላ እና ታሪካዊቷ ጎንደር ከተሞች ለሚጓዙ ተጨማሪ በረራዎችን ለመመደብ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታውቋል።
አየር መንገዱ፥ እነዚህ ክብረ በዓላት ከሀይማኖታዊ በዓልነታቸው ባለፈ ከተለያዩ የአለማችን ክፍሎች የሚመጡ ጎብኚዎች በስፋት የሚታደሙባቸው እንደመሆናቸው መጠን የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአየር በረራን በበቂ ሁኔታ በመመደብ የተለመደውን የተሳለጠ አገልግሎት ለመስጠት ተዘጋጅቷል ብሏል።
እነዚህ ተጨማሪ በረራዎች ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ ያለምንም መንገደኛ መሆኑን ታሳቢ ያደረገ የዋጋ ማስተካከያ በተጨማሪ በረራዎቹ ላይ ብቻ የሚደረግ መሆኑን ገልጿል።
በመሆኑም የሚደረገው የዋጋ ማስተካከያ ወደ ከተሞቹ የሚደረጉትን መደበኛ በረራዎች የማይመለከት መሆኑን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል።