የኮሪደር ልማቱ ለጥምቀት በዓል ክፍት ይሆናል- የጎንደር ከተማ አስተዳደር - ኢዜአ አማርኛ
የኮሪደር ልማቱ ለጥምቀት በዓል ክፍት ይሆናል- የጎንደር ከተማ አስተዳደር
ጎንደር፤ ታኅሣሥ 22/2017(ኢዜአ)፦ የጎንደር ከተማ የመጀመሪያው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት በጥምቀት በዓል ዋዜማ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆን ከተማ አስተዳደሩ ገለፀ።
የከተማው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው እንዳሉት የከተማው የኮሪደር ልማት ታሪክን፣ ቅርስን፣ ውበትንና የቀደመ የስልጣኔ አሻራን በጠበቀ መንገድ እየተካሄደ ነው።
በመጀመሪያው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት አንድ ነጥብ ስምንት ኪሎሜትር የሚያካልል መሆኑን ገልጸው፤ የነባር ሕንጻ ገጽታ ማሻሻል፣ የእግረኛ መንገዶች፣ የጎዳና ላይ መብራቶችና የአረንጓዴ ስፍራዎችን ያማከለ እንደሆነ ገልጸዋል።
የኮሪደር ልማቱ በጎንደር ከተማ በድምቀት ለሚከበረው የጥምቀት በዓል ልዩ ውበት እንደሚፈጥር ገልጸው፤ ለከተማዋ የኢኮኖሚ፣ የኢንቨስትመንትና የቱሪዝም እንቅስቃሴ እንደሚያነቃቃም ጠቁመዋል።
የአጼ ፋሲል አብያተ መንግስት አካባቢ የኮሪደር ልማት የቅርሱን ገጽታ ለማጉላትና ደህንነት ለመጠበቅ እንዲሁም የቱሪስት ፍሰትና ቆይታ በማራዘም ያግዛል ብለዋል።
በዚህም የመጀመሪያው ምዕራፍ ኮሪደር ልማት ለጥምቀት በዓል ዋዜማ ለጎብኚዎች ክፍት ይደረጋል ብለዋል።
ከፒያሳ እስከ አየር ማረፊያ ድረስ 12 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው ሁለተኛው ምዕራፍ የጎንደር ከተማ ኮሪደር ልማት በጥራትና በፍጥነት እየተከናወነ መሆኑን አስረድተዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ አማካሪ መስፍን አበጀ (ዶ/ር) የኮሪደር ልማቱ የጎንደር ከተማን ታሪካዊ እሴት የጠበቀና ዘመኑን የዋጀ እንደሆነ ገልጸዋል።
ጥንታዊቷ ጎንደር ታሪኳን የሚመጥን መሰረተ ልማቶች እንዳልነበሯት ገልጸው፤ አሁናዊ ስራዎችን አበረታችና ተስፋ ሰጪ ናቸው ብለዋል፡፡