ጎንደር ከተማን በኮሪደር ልማት ስራ በማዘመን ለቱሪስት ምቹ የማድረግ ስራ እየተሰራ ነው - አቶ ቻላቸው ዳኘው

አዲስ አበባ፤ ታህሣሥ 21/2017(ኢዜአ)፡- ጎንደር ከተማን በኮሪደር ልማት ስራ በማዘመን ለቱሪስት ምቹ የማድረግ ስራ እየተሰራ መሆኑን የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው ገለጹ።

የክልል፣ የጎንደር ከተማና የመከላከያ ከፍተኛ አመራሮች በከተማው እየተከናወነ ያለውን የኮሪደር ልማት የስራ እንቅስቃሴ ምሽቱን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።


 

በዚህ ወቅት የከተማዋ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ቻላቸው ዳኘው እንደገለጹት 1 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር የመጀመሪያ ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ለጥምቀት ለማድረስ እየተከናወነ ነው።

የኮሪደር ልማት ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል የፈጠረ እና በቀን እና በማታ የመስራት ባህልን የፈጠረ መሆኑንም ተናግረዋል።

በመጀመሪያው ምዕራፍ የመንገድ፣ የፍሳሽ ማስወገጃ ድሬኔጅ፣ የመብራት ዝርጋታ፣ የሳር ተከላ እና ሌሎች ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አክለውም ለሁለተኛው ምዕራፍ ስራም ቦታዎች የማፅዳት፣ ካሳ እና ትክ የሚያስፈልጋቸው የልማት ተነሺዎች እየተስተናገዱ መሆኑን ተናግረዋል።

ጎንደር የቱሪስት ከተማ ናት፤ ከተማዋን በኮሪደር ልማት በማዘመን ለቱሪስት ምቹ የማድረግ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ነው የገለጹት።

በወርሀ ጥር ጎንደር በጥምቀት የምትደምቅበት ወቅት መሆኑን አስታውሰው በዘንድሮው የጥምቀት በዓል ከ1 ሚሊዮን በላይ እንግዶች ሊሳተፋ እንደሚችሉ ገልጸዋል።


 

ለጥምቀት በዓል ለሚመጡ እንግዶች ከተማውን በማስዋብ በቆይታቸው ጥሩ ጊዜ እንዲያሳልፉ ለማስቻል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የአማራ ክልል የርዕሰ መስተዳድሩ የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ዘርፍ አማካሪ መስፍን አበጀ(ዶ/ር) በበኩላቸው የጎንደርን ታሪክና እሴት የጠበቀ ዘመናዊ የኮሪደር ልማት እየተከናወነ መሆኑን መመልከታቸውን ገልጸዋል።

ጎንደር ቀደምት ከተማ ብትሆንም በፌዴራልና በክልል ትልልቅ ፕሮጀክቶች እንዳልነበራት ገልፀው አሁን ላይ ታሪኳንና ህዝቧን የሚመጥን ስራ እየተከናወነ ነው ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።

በጎንደር ከተማ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት የስራ ባህልን ያዳበረና ለሌሎች ከተሞች ተሞክሮ እንደሚሆንም መግለጻቸውም ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም