ቀጥታ፡

የዲፕሎማሲ ስኬት ከአዲስ አበባ እስከ አንካራ

ኢትዮጵያና ሶማሊያ በአንካራ ያደረጉት ስምምነት በአፍሪካ ቀንድ የሰላም እና የልማት ትብብርን ለማጠናከር እንደማሳያ ይወሰዳል፡፡

ምንም እንኳን ከራሳቸው የግል ስውርና የገሀድ ፍላጎት መነሻነት የሁለቱን ሀገራት ስምምነት ሊያጣጥሉ የሚሞክሩ አንዳንድ የውጭ ሀይሎች ቢኖሩም የአንካራው ስምምነት ከሁለቱ ሀገራት ፍላጎትና ጥቅም የተሻገረ ቀጣናዊ ትሩፋት ያለው ነው።

የአንካራው ስምምነት ይዘቶች፣ ለሁለቱ ሀገራት እና ለቀጣናው የሚኖረው በረከት እና የስምምነቱን ተፈጻሚነት የማይፈልጉ ሃይሎች አካሄድ ምን እንደሚመስል እንዲሁም ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላም፣ ልማትና ትብብር ላይ እስካሁን ያደረገችውን አበርክቶ ለመቃኘት እንሞክር።

ኢትዮጵያ በአፍሪቃ ቀንድ ቀጣና

የአፍሪካ ቀንድ ከ170 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የሚኖርበት ቀጣና ነው።

ቀንዱ ከቀይ ባሕርና ሕንድ ውቅያኖስ የሚያገናኘውን የዓለማችን ስትራቴጂካዊ ስፍራ በመያዙ ለዓለም የስበት ማዕከል ሆኗል።

ቀጣናው ፖለቲካዊና ምጣኔ ሀብታዊ ጠቀሜታው ጉልህ ነው። በቀይ ባህር በየዓመቱ በሺህዎች የሚቆጠሩ መርከቦች እንደሚተላለፉበት መረጃዎች ያመላክታሉ።

የዓለምን 12 በመቶ የወደብ ገበያ ይሸፍናል። በዚህም ምክንያት ብሄራዊ ጥቅማቸውን ለማሳካት የሚሹ የሩቅም የቅርብም ጠላትና ወዳጅ ሀገራት አካባቢውን ለመቃኘት የሚያባክኑት ሽርፍራፊ ሰከንድ የለም። ሁሌም በአካባቢው የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን አይናቸውን ሳይነቅሉም ክትትል የሚያደርጉበት ቀጣና ነው።

ቀጣናው የሃያላን ቀጥተኛና ኢ-ቀጥተኛ ዕጆች የሚበዙበት በመሆኑም ቀጣናውን ኢ-ተገማችና ተለዋዋጭ መልክ እንዲይዝ አድርጎታል።

ይህ ደገሞ ለቀጣናው ሁለንተናዊ ልማትና ትብብር ዋጋ እየከፈለች ላለችው ኢትዮጵያ ፈተና መደቀኑ ዕሙን ነው።

ኢትዮጵያም ለቀጣናው ሁለንተናዊ ትስስር፣ ሰላምና ትብብር በየዘመኑ ከፍተኛ ዋጋ ስትከፍል ቆይታለች።

ለአብነትም በመሰረተ ልማት ረገድ በድንበር ተሻጋሪ የባቡር፣ የመንገድ እና የኤሌክትሪክ ኃይል መሰረተ ልማት በማስተሳሰር በኩል የኢትዮጵያ ሚና ከማንም የላቀ ነው።

ኢትዮጵያ በአፍሪካም ሆነ በዓለም ሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ላይ በመሳተፍ ለሰላም እና ለነጻነት መከበር ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት ለአፍሪካ ብሎም ለዓለም ሰላምና ደህንነት መከበር የላቀ ውለታ ውላለች።

በተለይም በምስራቅ አፍሪካ ለጎረቤት ሀገራት ሠላም መጠበቅ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍላለች። ሶማሊያ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ለዚህ አብነት የሚሆኑ ሀገራት ናቸው።

ለሀገራቱ ሰላም መከበር በከፈለችው ዋጋም ሀገራቱ ከግጭት ቀውስ እንዲወጡ፣ መንግሥታቱ በሁለት እግራቸው እንዲቆሙ አድርጋለች።

ሶማሊያ አጣብቂኝ ውስጥ በገባችበት ወቅት ሁሉ ኢትዮጵያ በሚቀብላት ጥያቄ መሰረት አልሻባብን በመዋጋት ህዝቡን ከዕልቂት ሀገሪቱንመ ከመበታተን ታድጋለች።

ኢትዮጵያ ለሀገራት ሰላምና ደህንነት ለተጫወተችው ሚናም ዓለም አቀፍ ዕውቅና ተችሯታል። ዛሬም ለቀጣናው ሠላም፣ የጋራ ልማትና ትብብር ሌት ተቀን እየሠራች ትገኛለች።

በቅርቡ ከሶማሊያ ጋር የተደረሰው የአንካራው ስምምነት ኢትዮጵያ ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ያላትን የጸና አቋምና ቁርጠኝነት ያሳየችበት የዲፕሎማሲ ድል ነዉ።

የአንካራው ስምምነት-የዲፕሎማሲ ስኬት ማሳያ

በያዘነው ታኅሣሥ ወር መባቻ ላይ በቱርኪዬ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶሃን አሸማጋይነት የተደረገው የአንካራ ስምምነት በኢትዮጵያና ሶማሊያ መካከል ተፈጥሮ የነበረውን አለመግባባት የቀረፈ ስምምነት ነው።

ስምምነቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ሰላምና ትብብርን የሚያጎለብት፣ የሀገራቱን ሕዝቦች ትስስር ይበልጥ የሚያጠናክር፣ ለቀጣናው ሰላም፣ ልማትና ብልጽግና የሚበጅ ሲሉ በርካቶች ታሪካዊ ስምምነት እንደሆነ ገልጸዋል።

የአፍሪካ ሕብረት፣ የአውሮፓ ሕብረትና ኢጋድ አድንቀውታል። እንግሊዝ፣ ጀርመንና አሜሪካን ጨምሮ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ስምምነቱ ለቀጣናው ያለውን ፋይዳ በማውሳት አሞካሽተውታል።

በኢትዮጵያ በኩል ደግሞ ሀገሪቱን ወደቀይ ባህር የመለሰ ታሪካዊ የዲፕሎማሲ ድል ተሰኝቷል። በቀጣናው ሰላም የከፈለችውን ዋጋም ዕውቅና ያሰጠ ነው።

የአንካራ ስምምነት ኢትዮጵያ የባህር በር እንድታገኝ ለምታደርገው ጥረት በር ከፋች ሆኗል። በዚህም የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት መሻት ዓለም አቀፍ ዕውቅና እንዲያገኝ አስችሏል። በዚህም የኢትዮጵያ የወደብ ጥያቄ ህጋዊ ሞራላዊ እና ፖለቲካዊ መሰረት ያለው ነው።

ይህም ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ ስኬት ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡ የዘርፉ ምሁራንም ስምምነቱ ከሁለቱ ሀገራት ባሻገር ለወዳጅ ሀገራት ጭምር ተስፋ የፈነጠቀ ክስተት ነው፡፡

ስምምነቱ ለአደራዳሪዋ ቱርኪዬ ጭምር የዲፕሎማሲ ተቀባይነቷን ያሳደገ ነው። ቱርኪዬ በአፍሪካ ቀንድ ለምታደርገው ተሳትፎ መሸጋገሪያ ድልድይ እንደሚሆናት ተንታኞች ይናገራሉ።

በጥቅሉ ስምምነቱ ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው በመጥቀስ ኢትዮጵያ ሚዛን የሚደፋ ድል እንድትቀዳጅ አስችሏታል ይላሉ።

የፀረ-አንካራ ስምምነት ሃይሎች

ስምምነቱ ቀጣናውን ለማተራመስ ስውር ዓላማ ሰንቀዉ ለሚንቀሳቀሱ አካላት ራስ ምታት ሆኗል። ዓለም በአንድ ድምጽ ያደነቀውን፣ የቀጣናውን ሠላም በማስጠበቅ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት የዓለም ሀገራት እና የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች እየመሰከሩለት ያለውን ይህን ስምምነት ከአላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት ለመጠበቅ የሁሉንም ርብርብ  ይፈልጋል፡፡

ስምምነቱ የቀጣናውን ሰላም እና መረጋጋት የማይሹ አካላት እኩይ አላማ ያከሸፈ ነዉ፡፡ ሆኖም እነዚህ አካላት በሚያገኙት አጋጣሚ ሁሉ ስምምነቱ ግቡን እንዳይመታ መጣራቸው የማይቀር ነው፡፡

የሁለቱ ሀገራት ስምምነት እንዳይሰምርም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሶማሊያ ላይ በሚያሳድሩት አሉታዊ ጫና ዋና እና ተጎጂ ሶማሊያ እና የሶማሊያ ህዝብ መሆናቸው የእነዚሁ አካላት የቀደሙ ጣልቃ ገብነቶች ያስከተሉት ጉዳት ጥሩ ማሳያዎች ናቸው፡፡

እነዚህ ሃይሎች ለሶማሊያውያን አንድነት እና ሰላም ከፍተኛ ዋጋ የከፈለውን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በማጥላላት በየሚዲያዎቻቸው የሚያናፍሱት መሰረተ ቢስ መረጃ በሁለቱ ሀገራት ስምምነት እኩይ አላማቸው ላይሳካ በአጭር መቀጨቱን የሚያሳይ ነው::  

የአንካራውን ስምምነት ተከትሎ ከሶማሊያ ጋር ያላቸውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንደሚያጤኑት መግለፃቸው በአሸዋ መሰረት ላይ የገነቡት ሴራ መፍረሱን የሚያመላክት ሆኖም ታይቷል፡፡

እነዚህ አካላት ሶማሊያ በከፋ የውስጥ ችግር ውስጥ በነበረችበት ወቅት አይተው እንዳላየ ሲያልፉ ቢቆዩም የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ግን ለሶማሊያ መጠናከር እና የውስጥ ሰላም መስፈን የሚያደርጉት ድጋፍ ጊዜ እንደማይሽረው እና ጥቅም እንደማይለውጠው በተግባር የታየ ሀቅ ነው፡፡

የአንካራው ስምምነትም በደምና በመስዋዕትነት የተሳሰረው የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ወንድማማችነት ቢቀጥንም የማይበጠስ መሆኑን አመላካች ነው ላይበጠስም ተቋጥሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም