ቀጥታ፡

መንግስት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም መፍጠር እና ሁሉን አሳታፊ የሆነ ሀገረ መንግስት መገንባት የሚያስችሉ ዘላቂ የመፍትሄ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛል - ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ታህሳስ 21/2017(ኢዜአ)፡- መንግስት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም መፍጠር እና ሁሉን አሳታፊ የሆነ ሀገረ መንግስት መገንባት የሚያስችሉ ዘላቂ የመፍትሄ እርምጃዎችን በመውሰድ አዲስ የለውጥ ባህል እየፈጠረ እንደሚገኝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር) ገለጹ።

ሚኒስትሩ ”ኢትዮጵያ ኢን ፎከስ” በተሰኘው ፕሮግራም “የፖለቲካ እና ማህበራዊ ፈተናዎችን በዘላቂ መፍትሄዎች መፍታት” በሚል ርዕስ በተዘጋጀው ክፍል ሁለት ቃለመጠይቅ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ሚኒስትሩ በቆይታቸው በኢትዮጵያ የሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደት ከአፍሪካ አህጉር ካለው ነባራዊ እውነታ አንጻር የተለየ እንደሆነና የሂደቱ ባለቤት ሀገር በቀል የፖለቲካ ኃይሎች መሆናቸውን አመልክተዋል።

በአፍሪካ የሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደቱ በአብዛኛው የውጭ ተዋንያን ተጽእኖ ያረፈበት መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይሎች የሀገረ መንግስት ግንባታ ሂደቱን በማህበራዊ ውል ባለማሰራቸው ምክንያት ችግሮች ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፉ ምክንያት ሆኗል ነው ያሉት።

አምባገነንነት እና የኃይል እርምጃ መገለጫው የነበረው የፖለቲካ ባህል ለዴሞክራሲያዊ እና ለሰላማዊ ትግል አማራጭ ቦታ እንዳልነበረው አስታውሰዋል።

የሕዝብ ብሶቶች እና ቅሬታዎችን ለመፍታት ይወሰዱ የነበሩ እርምጃዎች ይበልጥ ታሪካዊ ቁርሾና መከፋፈልን መፍጠራቸውን ነው ሚኒስትሩ የገለጹት።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የሚመራው የለውጡ አመራር ወደ ስልጣን ከመጣበት ጊዜ አንስቶ ይሄን ችግር ለመፍታት የተለያዩ ሪፎርሞች ማድረጉን አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የታጠቁ ኃይሎች ወደ ሰላማዊ አማራጭ እንዲመጡ ባቀረቡት ጥሪ መሰረት ታጣቂዎች መሳሪያቸውን በማስቀመጥ ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ መምጣታቸውን ተናግረዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰላም ጥሪና አቋም ወጥነት የነበረውና ሁሌም ከሰላማዊ ትግል ውጪ ኃይል አማራጭ መሆን እንደማይችል የሚጠቁም የነበረና ይህም በተግባር መታየቱን ነው ሚኒስትሩ ያመላከቱት።

መንግስት የኃይል አማራጭን በሚከተሉ አካላት ሕግን የማስከበር እርምጃ መውሰዱን ገልጸው በጸጥታና ደህንነት ተቋማት ላይ የተወሰዱ ማሻሻያዎች የነበሩ በርካታ ፈተናዎችን መቋቋም ያስቻሉ ናቸው ብለዋል።

የጸጥታ ዘርፉ ሪፎርም ጠንካራ ተቋማትን በመገንባት ኢትዮጵያን በማስቀጠል ረገድ ጉልህ ሚና መጫወቱን አንስተዋል።

መንግስት የህግ የበላይነትን ማስከበር ብቻ ዘላቂ መፍትሄ እንደማያመጣ በማመን ከታጠቁ ኃይሎች ጋር በመወያየት ችግሮች እንዲፈቱ ጥረት ማድረጉንና በዚህም ውጤቶች መገኘታቸውን ገልጸዋል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ታጥቀው ከሚንቀሳቀሱ ሀይሎች ጋር የተደረጉ የሰላም ስምምነቶችን ሚኒስትሩ በማሳያነት ጠቅሰዋል።

መንግስት ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋትን ለማምጣት በሶስት ቁልፍ ጉዳዮች ላይ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝም ነው የገለጹት።

የቀድሞ ታጣቂዎችን ትጥቅ በማስፈታት ወደ ሰላማዊ ህይወት እንዲመለሱ የማድረግ ፕሮግራም(ዲዲአር) ከስራዎቹ መካከል አንዱ መሆኑን አንስተዋል።

በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት አማካኝነት ለቀድሞ የትግራይ ክልል ታጣቂዎች የተሃድሶ ስልጠና በመስጠት ወደ መደበኛ ኑሯቸው እንዲመለሱ እየተደረገ መሆኑን ገልጸው ፕሮግራሙ ሁሉን አቀፍ በሆነ መልኩ እየተተገበረ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በሌላ በኩል በፍትሕ ሥርዓት በደሎችን በማከም ሰላምና ዴሞክራሲ የሰፈነባት ሀገር መገንባትን ባለመ መልኩ የሽግግር ፍትሕ ሥርዓትን ለመተግበር የሚደረገው ጥረት አካል የሆነው የሽግግር ፍትህ ፖሊሲን አስመልክቶ ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል።

የሽግግር ፍትሕ በሕዝቦች መካከል መተማመንና ዘላቂ ሰላምን ለመፍጠር ሁሉንም የሚያሳትፍ፣ የሕግ ተጠያቂነት፣ ፍትሕ፣ እርቅና ካሳን ጭምር ታሳቢ የሚያደርግ መሆኑን አመልክተዋል።

ይህ ሂደት የኢትዮጵያን ያለፈ መጥፎ የታሪክ ምዕራፍ ዘግቶ አዲስ ምዕራፍ ለመክፈት ያስችላል ነው ያሉት።

ስር የሰደዱ አለመግባባቶች፣ ግጭቶች እና ታሪካዊ ቁርሾዎች በውይይት የመፍታት ግብ ባለው የሀገራዊ ምክክር ሂደትም ግልጽ፣ ሁሉን አሳታፊ እና ነጻ በሆነ መልኩ እየተካሄደ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የምክክር ሂደቱ ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት፣ አሳታፊ የፖለቲካ ባህልን ለመፍጠር እና ለሀገር ግንባታ ቁልፍ ሚና እንዳለውም ነው ያብራሩት።

መንግስት ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ፈተናዎችን ከዚህ ቀደም ከተለመዱ አካሄዶች በመውጣት ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት እያከናወነ ያለው ስራ ፍሬ እያፈራ መሆኑንም ሚኒስትሩ በቆይታቸው አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም